በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተስማሙ


የአውሮፓ ኮምሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ በብራስልስ፣ ቤልጂየም እአአ ግንቦት 31/ 2022
የአውሮፓ ኮምሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ በብራስልስ፣ ቤልጂየም እአአ ግንቦት 31/ 2022

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች የሚበዛው የሩሲያ የነዳጅ ዘይት አቅርቦት እንዲጣል ትናንት ሰኞ ከመሸ ሥምምነት ላይ መድረሳቸው ተዘግቧል። መሪዎቹ ሥምምነት ላይ የደረሱት በብዛት ከሩሲያ በሚገባ ነዳጅ የሚጠቀሙ ሀገሮችን ኢኮኖም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሩሲያ ላይ የበለጠ ጫና ለማሳደር መሆኑ ተገልጿል። መሪዎቹ በተስማሙበት ማዕቀብ ሩሲያ በመርከብ የምትልከው ነዳጅ በሙሉ የሚታገድ ሲሆን በቧምቧ የምትልከው ግን በጊዜያዊነት ይቀጥላል።

የባህር በር የሌላት ሀንጋሪ የአባል ሀገሮችን ሙሉ ይሁንታ የሚጠይቀውን ውሳኔ እንደምትቃወም አስፈራርታ እንደነበር ይታወሳል። ይህ ማዕቀብ ጀርመን እና ፖላንድ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛት ለማቆም መስማማታቸውን ተከትሎ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ሩሲያ ከምትልከው ነዳጅ ዘጠና ከመቶውን እንዳትልክ ያደርጋታል።

የአውሮፓ ኮምሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን፣

"ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው። አሁን ደግሞ በቧምቧ በምትልከው በቀሪው በአስር ከመቶው ነዳጇ ጉዳይ ላይ እናተኩራለን።" ብለዋል።

ማዕቀቡ በሩሲያ ነዳጅ ላይ አብዝተው የሚተመማመኑትን ሀንጋሪ ቼክ ሪፐብሊክ እና ስሎቫኪያን አይመለከትም። የቭላዲሚር ፑቲን የቅርብ አጋር የሆኑት የሀንጋሪው ፕሬዚዳንት ቪክተር ኦርባን ለሳምንታት የህብረቱ ማዕቀብ እንዳያልፍ አድርገው መቆየታቸው ይታወሳል።

የዩክሬን መሪዎች ሩሲያ ለወረራዋ የምታውለውን ገንዘብ እንዳታገኝ ለማድረግ የነዳጅ ዘይት ንግዷ ሙሉ በሙሉ እንዲታገድ ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ትናንት ለአህጉራዊው ህብረት ባደረጉት ንግግር በድጋሚ ተማጽኖአቸውን አሰምተዋል።

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ለዩክሬን ኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ የሚውል 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ለመስጠት ተስማምተዋል።

በውጊያው አምባ ምስራቅ ዩክሬን ሲቬሮዶኔትስክ ከተማ ጎዳናዎች ላይ ከባድ ውጊያ እየተካሂደ ሲሆን የዩክሬን ኃይሎች የሩሲያ ኃይሎች የሚያወርዱትን ከባድ ጥቃት ለመመከት እየሞከሩ ናቸው።

በዋሽንግተን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን ሩሲያ ግዛት መድረስ የሚችል ሮኬት እንደማይልኩ ገልጸዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ብዛት ያለው ወታደራዊ እርዳታ የሰጠች ሲሆን ዩክሬን በይበልጥ ጠንካራ የሆኑ ሮኬቶች እንዲላኩላት ጠይቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ ወረራ ከከፈተች ወዲህ ዩክሬን ውስጥ ሰላሳ ሁለት የመገናኛ ብዙሃን አባላት መገደላቸውን ፕሬዚደንት ዘለንስኪ ተናግረዋል። ትናንት የሠላሳ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ሌክሬክ ኢምሆፍ ሲቮሮዶኔትስክ ከተማ ውስጥ ተገድሏል።

XS
SM
MD
LG