ኡጋንዳ ወደ ምሥራቅ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ 1000 የሚሆኑ ወታደሮቿን ትልካለች ሲሉ የሃገሪቱ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ዛሬ አስታውቀዋል።
ምሥራቅ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በኮንጎ ሠራዊትና ኤም 23 በተባሉት አማጺያን መካከል በሚደርግ ውጊያ እየተናጠ ያለ ቦታ ነው።
በዚህም ምክንያት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የተሰኘውን ስብስብ ሁከቱን ለማስቆም የቀጠናውን የጋራ ጦር ወደ ሥፍራው እንዲልክ አስገድዶታል።
ኬንያ ከሳምንት በፊት ወደ አካባቢው ጦሯን ልካለች።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትንሿ ጎረቤቷ የሆነችውን ሩዋንዳ የኤም 23 ጦርን ትረዳለች ብላ በመወንጀሏ በአካባቢው ውጥረት ሰፍኗል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎችም ሩዋንዳ አማጺያኑን መደገፏን ደርሰንበታል ብለዋል።
ውንጀላውን በማስተባበል በሩዋንዳው የዘር ፍጅት ማግስት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመሠረተን አንድ የሁቱ አማጺ ቡድን ትረዳለች ስትል ኪጋሊ ኪንሻሳን መልሳ ትከሳለች።
በአብዛኛው በኮንጎ ቱትሲ ሚሊሺያ የተዋቀረው ኤም 23 የተሰኘው አማጺ ሃይል በሰሜን ኪየቩ ግዛት ሰፊ ቦታዎችን የተቆጣጠረ ሲሆን ጎማ ወደተባለችው ሌላዋ የኮንጎ ትልቅ ከተማ እየተጠጋ መሆኑ ተሰምቷል።
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሁለት የኡጋንዳ ወታደራዊ ምንጮች ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ካምፓላ የመረጃ፣ የህክምና እንዲሁም የአቅርቦት ቡድኗን ቀድማ ወደ ጎማ ልካለች።
የኤም 23 አማጺ ቡድን ከ10 ዓመት በፊት ጎማን ለጥቂት ግዜያት ሲቆጣጠር ተሰሚነት አግኝቶ ነበር። ወዲያው በመጠቃቱ ግን አፈግፍጎና ተደብቆ ቆይቶ ነበር።
ተዋጊዎቼ በሥምምነቱ መሠረት ወደ ዋናው የሃገሪቱ ጦር አልተቀላቀሉም በሚልና ሌሎች ቅሬታዎች ምክንያት አማጺያኑ ባለፈው ዓመት ተመልሰው ብቅ ብለዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰ ጦር ኬንያ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳን፣ እና ደቡብ ሱዳንን እንደሚያካትት ይጠበቃል።