ዋሽንግተን ዲሲ —
የዩጋንዳ ፖሊሶች ባለፈው ማክሰኞ ዋና ከተማዋ ካምፓላ ውስጥ የደረሰውን የቦምብ ፍንዳታ ካደረሰው ጽንፈኛ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው የወነጀሉዋቸውን ቢያንስ አምስት ሰዎች መግደላቸውን አስታወቁ።
አራቱ ወንዶች የተገደሉት ከኮንጎ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ በምትገኝ ከተማ በኩል ተመልሰው ዩጋንዳ ሊገቡ ሲሞክሩ መሆኑን ፖሊሶቹ ገልጸዋል። አምስተኛው የእስልምና ሃይማኖት መምህር መሀመድ ኪሬቩን ደግሞ ካምፓላ አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መግደላቸውን ፖሊስ አስታውቋል:: አንድ ሌላ የእስልምና መምህር ሱሊማን ኒሱቡጋን በማደን ላይ ነን ብሏል።
ሁለቱ ሰዎች ሙስሊም ወጣት ወንዶችን ጽንፈኝነት እየሰበኩ የኃይል ጥቃት የሚያደርሱ ሚስጥራዊ ህዋሶች ውስጥ እንዲገቡ በማበረታታት ተወንጅለዋል።
ማክሰኞ እለት ቢያንስ አራት ሰዎች ለተገደሉባቸው የቦምብ ጥቃቶች እስላማዊ መንግሥት ብሎ ራሱን የሚጠራው ቡድን በዩጋንዳውያን እንደተፈጸመ ገልጾ ኃላፊነት ወስዷል። የዩጋንዳ መንግሥት ባለሥልጣናት በበኩላቸው የአይኤስ ተባባሪ የሆነው የተባበሩት ዲሞክራሲያዎ ኃይሎች የተባለውን ቡድን ለፍንዳታዎቹ ተጠያቂ አድርገዋል።