ዋሽንግተን ዲሲ —
ዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ውስጥ ትናንት ማክሰኞ ከደረሱት እና ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ሽብርተኛ ቡድን ኃላፊነት ከወሰደባቸው ሁለት ፍንዳታዎች ተከትሎ የቦምብ ጥቃቶች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ የጸጥታ ባለሥልጣናቱ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
በፍንዳታዎቹ ሁለት ሲቪሎች እና አንድ ፖሊስ ሲገደል ሰላሳ ሦስት ሰዎች ቆስለዋል። ከቆሰሉት መሃል አንዳንዶች በአስጊ ሁኔታ የተጎዱ መሆናቸው ተገልጿል።
ፈንጂ የያዙ አጥቂዎች ካምፓላ ውስጥ በፓርላማው ህንጻ እና አንድ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ባደረሱት ፍንዳታ ሦስት አጥፍቶ ጠፊዎች መሞታቸውንም ፖሊስ አስታውቋል። ፖሊስ መጀመሪያ ላይ ፍንዳታውን ያደረሰው የተባበሩት ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች የተባለው ጽንፈኛ ቡድን እንደሆነ ተናግሮ ነበር።
ሦስተኛ ጥቃት ሳይደርስ ለማክሸፍ እንደተቻለ የገለጹት የዩጋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባይ ቦምብ ሊያፈነዳ ሲያደባ የነበረ አጥፍቶ ጠፊ ተብሎ የተጠረጠረ ሰው ፖሊስ ተከታትሎ እንደያዘ አመልክተዋል።
የዩጋንዳ ባለሥልጣናት በቅርብ ሳምንታት በሃገሪቱ በተከታታይ የደረሱትን የቦምብ ፍንዳታዎች ተከትሎ በንቃት እና በጥንቃቄ እንዲከታተል አሳስበዋል።