ኡጋንዳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን (ተመድ) የሰብአዊ መብቶች ቢሮ በአገሯ የሚያደርገውን ሥራ እንዲቋረጥ የእድሳት ፈቃድ በመከልከል ያገደች መሆኑ ተነገረ፡፡
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥር 26/2015 ካምፓላ ውስጥ ለሚገኘው በኡጋንዳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር በጻፈው ደብዳቤ “በመላ አገሪቱ የሰብአዊ መብቶችን ለማስተዋወቅና ለመቆጣጠር የሚያስችል በቂ አቅም የተገነባ በመሆኑ” የቢሮው ሥራ ፈቃድ የማይታደስ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በካምፓላ የሚገኘው የተመድ የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ኡጋንዳ ውስጥ በአንዳንድ የአገር ውስጥ የመብት ተሟጋቾች እና ሌሎች ተቋማት በመንግሥት የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን አስመልክቶ የሚያቀርቧቸውን ተቃውሞዎችን ሲያጎላ እንደነበር የኦሶሴይትድ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የተቃዋሚ ድርጅት መሪ ቦቢ ዋይን፣ ብዙዎቹ ደጋፊዎቻቸው በህገወጥ መንገድ ታስረው የሚገኙ መሆናቸውን በመግለጽ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብአዊ መብቶችን አስመልክቶ በኡጋንዳ መንግሥት ላይ ተጽእኖውን እንዲያሳርፍ ጠይቀዋል፡፡
እኤአ ከ2006 ጀምሮ ኡጋንዳ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የቆየው የተመድ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የታገደው በኡጋንዳ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሰ በመጣበት ጊዜ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
እኤአ በ2021 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ወከባ ይደርስብናል ያሉትን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመዘገብ፣ ወደ ተቃዋሚ ጽ/ቤቶች የሄዱ ጋዜጠኞችን፣ ፖሊሲ ሲያዋክብ እንደነበርም ተዘግቧል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስ የደህንነት አጋር የሆኑት የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቪኒ እኤአ ከ1986 ጀምሮ ላለፉት 37 ዓመታት ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ሮይተርስ አመልክቷል፡፡