ቱኒዚያ የ”ሽብር” ቡድን ስትል የገለጸቻቸውንና በሴቶች ብቻ የተመሠረተን ዘጠኛ አባላት ያሉት ቡድን፣ አንድ የመንግሥት ሚኒስትርን ለመግደል አሲረዋል በሚል ዘብ ጥያ አውርዳለች።
በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ለመጀመሪያ ግዜ የታወቀና ሁሉም ዓባላት ሴቶች የሆኑበት የጂሃዲስት ቡድን እንደሆነ ከተገለጸው ውስጥ ሁለቱ መሪዎች በ25 ዓመት እሥራት ሲቀጡ ሌሎቹ ደግሞ ከ3 እስከ 14 ዓመት ተቀጥተዋል። አንዲት ዓባላቸው ነጻ ተለቃለች።
ቅጣቱ የተላለፈው በመዲናዋ ቱኒስ በሚገኝ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የኤኤፍፒ ሪፖርት ጠቅሷል።
ክሱ የተጀመረው ከአምስት ዓመታት በፊት በእአአ 2016 ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በወቅቱ የአገር ውስጥ ሚኒስትር የነበሩትን ሄዲ ማጅዱብ ቤተሰቦቻቸውን በሚጎበኙበት ወቅት ለመግደል ሞክረዋል የሚል ወሬ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረ ሲሆን፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ግን ወሬውን አስተባብሏል።
አንዷ የቡድኑ ዓባል የሚኒስትሩ ወላጆች ጐረቤት በመሆኗ መረጃውን አስተላልፋለች ሲል እንድ የአገር ውስጥ ሬዲዮ ዘግቧል።
የቤን አሊ መንግስት ከ12 ዓመታት በፊት በአመጽ ከተወገደ በኋላ፣ ቱኒዚያ ውስጥ ተከታታይ የጂሃዲስቶች ጥቃት ተስተውሏል። በጥቃቱም በደርዘን የሚቆጠሩ ፀጥታ አስከባሪዎችና አገር ጎብኚዎች ተገድለዋል።
ጂሃዲስቶቹን በማክሰም ረገድ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።