በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራዩ ቀውስ ወደ ሱዳን የሚሰደዱ ዜጎች እየጨመሩ ነው


በግጭቱ መባባስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው
በግጭቱ መባባስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው

የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ድርጅቶች በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በተባባሰው ወታደራዊ ግጭት የሰብአዊ ቀውስ እየጨመረ መመጣቱን እየገለጹ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እስከ 30 ሺ የሚጠጉ ዜጎች ወደ አጎራባች አገሮች መሰደድ መጀመራቸውና ቁጥራቸውም በእየለቱ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደግሞ በዛሬው እለት “የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሰደዱ ወገኖችን ለመቀበል እና ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን” ገልጸዋል፡፡ የቪኦኤ ዘጋቢዎች ሊዛ ሽላይንና ማርጋሪት በሽር እንዲሁም የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባዎችን በማጠናቀር ዘገባ አዘጋጅተናል፡፡

በትግራይ ክልል፣ ሳምንት ባለፈው ወታደራዊ ግጭት፣ ኢትዮጵያውያን ሲቪል ዜጎችንና በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ደህንነት መከላከል፣ ለሰብአዊ መብት ተከታታዮች ዘንድ አብይ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የሰአብዊ ጉዳዎች አስተባባሪ እንደሚሉት፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሆኑስ ሰዎች፣ የሚሰጡት የሰብአዊ ነክ እርዳታዎች ተቋርጠዋል፡፡ የጸጥታው መደፈርስ፣ የምግብ፣ የጤና አቅርቦትና፣ ሌሎች መሰል እርዳታዎች እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ቃል አቀባይ የሆኑት ፣ ባባር ባለክ፣ ግጭቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ፣ ወደ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ደህንነት፣ አደጋ ላይ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“በዚህ መካከል በትግራይ ውስጥ ለ96ሺ ኤትራዊያን ስደተኞች የሚሰጠው እርዳታ አሳሳቢ በሆነ መንገድ ተቋርጧል፡፡ በዚያ ላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ተጨምረዋል፡፡” ብለዋል፡፡

የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እንደሚሉት፣ ትግራይ ውስጥ መኖርም ሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የበለጠ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የሚቋረጠው መብራት፣ ያለው የምግብ እጦት፣ እየጨመረ ያለው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት፣ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረው ነው፡፡ በዚያ ላይ፣ የግንኙነት መስመሮች ስለተቋረጡ ፣ መረጃዎችን መለዋወጥ አልተቻለም፡፡ ባለክ እንደሚሉት፣ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ጉዳይና የሰብአዊ እርዳታዎች መጓደል፣ በርካታ ሰዎችን፣ ወደ አጎራባች የድንበር አካባቢዎች እንዲሰደዱ አሰገድዷቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ከ14ሺ500 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ግማሾቹ ህጻናት ሲሆኑ ሁሉም ሱዳን ገብተዋል፡፡ ሌሎችም በርካታ ስደተኞች መንገድ ጀምረዋል፡፡ እንዲህ ይላሉ ባለክ

“እዚህ የደረሱት ሰዎች ይዘው የመጡት ትንሽ ነገር ብቻ አንጠልጥለው ነው፡፡ ይህም ስደተኞቹ ምን ያህል በጥድፊያ ብድግ ብለው እንደመጡ ያሳያል፡፡ ህጻናት ደክመውና ፈርተው ይታያሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የረድኤት ድርጅትና አጋሮቻችን እርዳታዎችን በፍጥነት ለማድረስ እየሰሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ግን፣ በላይ በላዩ የሚመጡት አዳዲስ ስደተኞች፣ በእጃችን ላይ ካለው እርዳታ በላይ እየሆኑ ነው፡፡” ብለዋል ባለክ፡፡

ባለክ እንደሚሉት፣ የሱዳን ባለሥልጣናት፣ አሁን የመጡትንም ሆነ ወደፊት ሊጨምሩ ይችላሉ የተባሉትን ስደተኞች የሚያሰፍር፣ የመጠለያ ካምፕ እያቋቋሙ ነው፡፡ አሁን ያለው ወደ 20ሺ የሚጠጉ ሰዎች የሚያስፈር ሲሆን፣ ከድንበሩ 80 ኪሎሜትር ያህል ርቆ ይገኛል፡፡ ሌሎችም ተጨማሪ ማስፈሪያ ቦታዎች የተመረጡ መሆናቸውንም ባለሥልጣኑ ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው እለት፣ በተባበሩት መንግሥታት የቪኦኤ ዘጋቢ ማርጋሪት በሽር፣ የተባበሩት መንግሥታትን ቃለ አቀባይ፣ ስቴፈን ዱጃሪክን አነጋግራ እንደዘገበችው ደግሞ ፣ ወደ 25ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን፣ ድንበር አሳብረው ወደ ሱዳን ገብተዋል፡፡ ይህ ቁጥርከ30ሺ በላይ መድረሱ ሲዘገብ፣ ዛሬ የወጣው የዓለም አቀፍ ረድኤቱ ድርጅት( UNHCR) ኃላፊዎች መግለጫ እንደሚያሳየው፣ በየቀኑ ወደ ሱዳን የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር፣ ወደ አራት ሺ እየተጠጋ መሆኑን ያሳያል፡፡

የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት ዋና ጸሀፊ፣ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ፣ ለየአገራቱ መሪዎች ስልክ ሲደዉሉ መቆየታቸውንም ጠቅሰው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞቻቸውም፣ እልባት ለመሻት በአካባቢው እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡ ለዋና ጸሀፊው፣ ከሁሉም በላይ የሰአብአዊ መብቶች፣ የሲቪል ዜጎች፣ ከአደጋ መጠበቅና፣ የሰብአዊ እርዳታዎች ተደራሽነት ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች መሆናቸውን ስቴፈን ገልጸዋል፡፡ ውጥረትን አርግቦ ሰላምን ማስፈን ለእነዚህ ነገሮች ወሳኝ መሆናቸውንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡

አሶሼትድ ፕሬስ ያነጋገራቸውና በሱዳን፣ በከሰላና፣ አልካደኣሪፍ የሚገኙ በተባበሩት መንግሥታቱ የስደተኞች ድርጅት ተወካዮች ደግሞ እንደሚሉት፣ አብዛኞቹ ስደተኞች፣ ህጻናትና ሴቶች ሲሆኑ፣ ብዙዎቹ በድካም የዛሉ፣ የተጠሙና የተራቡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ተከዜ፣ በሱዳን ደግሞ ሰቲት እየተባለ የሚጠራውን ወንዝ፣ በጀልባ አቋርጠው ሲመጡ፣ የቻሉትም እየዋኙ መሻገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ስደተኞች ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ፣ በሱዳን የሚገኘው አክቲቪስቱ አብዱልረኽማን አዋድ አብዱልረኽማን፣ አብዛኞች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የስደተኞች ሰነድ ያልተመዘገቡ መሆኑን አመልክቷል፡፡ እየጨመረ ሊሄድ ከሚችለው ስደተኞቹን ሁኔታ አንጻር፣ ሁኔታውን በቶሎ ማስተናገድ የሚቻልበት መንገድ መፈጠር እንዳለበትም፣ አብዱልረኽማን አሳስቧል፡፡

የአልቃደአሪፍ ገዥ ሱሌማን አሊ፣ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት የተባበሩት መንግሥታትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ፣ ከሚጎርፈው የስደተኞች ቁጥር አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ በሱዳን የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ባለሥልጣናት ግን፣ ሁኔታውን በሚመለከት፣ ከሱዳን ባለ ሥልጣናት ጋር እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞቹ ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲም “ተፈናቃዮቹ አፋጣኝ እርዳታዎችን የሚሹ በመሆናቸው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እጁን በቶሎ እንዲዘረጋ እንጠይቃለን” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ፣ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ “የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሰደዱ ወገኖችን ለመቀበል እና ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን” ገልጸዋል፡፡ የተሰደዱ ንፁሀን ዜጎችን ንብረታቸውን ለመጠበቅ ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ እና ሲመለሱም ሰላማቸውን እንደሚያስጠብቁም አስታውቀዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

በትግራዩ ቀውስ ወደ ሱዳን የሚሰደዱ ዜጎች እየጨመሩ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:47 0:00


XS
SM
MD
LG