በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል በተጣሉ እና በተቀበሩ ተተኳሾች ፍንዳታ ከ140 በላይ ነዋሪዎች እንደሞቱ ተገለጸ


በትግራይ ክልል በተጣሉ እና በተቀበሩ ተተኳሾች ፍንዳታ ከ140 በላይ ነዋሪዎች እንደሞቱ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:21 0:00

በትግራይ ክልል በተጣሉ እና በተቀበሩ ተተኳሾች ፍንዳታ ከ140 በላይ ነዋሪዎች እንደሞቱ ተገለጸ

በትግራይ ክልል በተጣሉ እና በተቀበሩ ተተኳሾች፣ እስከ አሁን በተሰበሰበ ሪፖርት፣ የ143 ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት እንዳለፈ፣ የክልሉ የፈንጅ አምካኝ ቡድን አስታወቀ፡፡

ጉዳቱ፣ በሕፃናት እና በሴቶች ላይ በዝቶ እንደሚታይ የጠቀሰው ቡድኑ፣ አሁንም፣ ጥቂት በማይባሉ የክልሉ ቦታዎች ተተኳሾች በመኖራቸው፣ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ(UN-OCHA)፣ ከአሁን በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ በትግራይ ክልል በተቀበሩ እና በተጣሉ ተተኳሾች፣ በተለይ በሕፃናት እና በሴቶች ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደኾነ፣ ከሰብአዊ ርዳታ ሠራተኞች መረጃ ማግኘቱን ገልጾ ነበር፡፡

ባለፈው የካቲት ወር፣ በክልሉ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ዓዲ ሃገራይ አካባቢ በሁለት ቦታዎች፣ እንዲሁም በክልሉ ማእከላዊ ዞን እገላ ወረዳ ሁለት ቦታዎች፣ ተጥለው የነበሩ ተተኳሾች ፈንድተው፣ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ማቁሰሉን ለአብነት የጠቀሰው ማስተባበርያ ቢሮው፣ ከክልሉ የፈንጅ አምካኝ ቡድን ጋራ በመቀናጀት፣ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሠራ እንደኾነም ገልጿል፡፡

በትግራይ ክልል የማኅበራዊ ጉዳይ እና መልሶ ማቋቋም ቢሮ የሰብአዊ የፈንጅ ማምከን ቡድን አስተባባሪ አቶ ተስፋይ ኣብርሃ፣ የቅርቡን ጦርነት ተከትሎ፣ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በተጣሉ እና በተቀበሩ ተተኳሾች፣ እስከ አሁን በተሰበሰበ ሪፖርት፣ የ143 ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡ ከእኒኽም የሚበዙት ሰለባዎች፣ ሕፃናት እና ሴቶች እንደኾኑ፣ አስተባባሪው አክለው ገልጸዋል፡፡

አኀዛዊ የጉዳት መረጃው፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የተጠናቀረ እንደኾነ የገለጹት አቶ ተስፋይ፣ ከሰላም ስምምነቱም በፊት፣ በተቀበሩ እና በተጣሉ ተተኳሾች ጉዳት ይደርስ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡

ኀይለ ማርያም ሚላው፣ የ15 ዓመት አዳጊ ነው፡፡ የቆላ ተንቤን ወረዳ ጎረሮ ቀበሌ ነዋሪ ሲኾን፣ ባለፈው ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ከአባቱ ጋራ በእርሻ ሥራ ላይ እያለ፣ ተቀብሮ በነበረ ተተኳሽ ጉዳት ደርሶበት፣ በመቐለ ዓይደር ሪፌራል ሆስፒታል ሕክምናውን እየተከታተለ እንዳለ አግኝተነዋል፡፡

በወቅቱ እኔ እያረስኩ እንደነበር የገለፁት፤ ወላጅ አባቱ አቶ ሚላው ገብረ ማርያም “ልጄ ከኋላዬ እየተከተለ በጉልጓሎ ሥራ እያገዘኝ ነበር፡፡ በያዘው ዶማ ሲቆፍር፣ የፍንዳታ ድምፅ ሰማን፡፡ በፍንዳታው የግራ እጁ እንደምታየው ተቆርጧል፤ ግንባሩ እና ጭኑ አከባቢም ተመቷል፡፡” ብለዋል።

ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት፣ ከባድ ውጊያ የተካሔደበት አካባቢ እንደነበር ያወሱት አቶ ሚላው፣ ከአሁን በፊትም፣ በአካባቢው ተቀብሮ የነበረ ተተኳሽ ፈንድቶ፣ አንድ ልጅ ሲሞት፣ የሌላን ልጅ የዐይን ብርሃን ደግሞ አጥፍቷል፤ ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ማኅበራዊ ጉዳይ እና መልሶ ማቋቋም ቢሮ የሰብአዊ የፈንጅ ማምከን ቡድን አስተባባሪ አቶ ተስፋይ ኣብርሃ፣ በርካታ አካባቢዎች ገና ከተተኳሾች አለመጽዳታቸውን ገልጸው፣ ከመስከረም በኋላ የማምከኑ ሥራ በይፋ ሊጀመር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በእስከ አሁኑ የዳሰሳ ሥራ ትኩረት የተደረገው ግን፣ በትምህርት ቤቶች ላይ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ በበኩላቸው ፤ “እስከ አሁን፣ በ1ሺሕ720 ትምህርት ቤቶች ዳሰሳ ተካሒዷል፡፡ የተቀበሩ እንዲሁም በገላጣ መሬት ላይ እና በሣር ውስጥ የተጣሉ ከ8ሺሕ500 በላይ ልዩ ልዩ ተተኳሾች ተገኝተዋል፡፡ እነዚኽን፣ ከየትምህርት ቤቱ አጽድተናል፡፡” ብለዋል።

ባልመከኑ ተተኳሾች የሚደርሰው ጉዳት፣ በተለይ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የበዛ እንደኾነ፣ አቶ ተስፋይ አስረድተዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የተጣሉ እና የተቀበሩ ተተኳሾችን ሲያገኝ፣ አንዳችም የመነካካት ሙከራ ሳያደርግ፣ ለሚመለከተው የጸጥታ አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት፣ አሳስበዋል፡፡

በመቐለ ዓይደር ሪፌራል ሆስፒታል፣ ባልመከነ ተተኳሽ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰበት ልጃቸውን እያሳከሙ ያገኘኋቸው አቶ ሚላው፣ ሕዝብ ያለስጋት በነፃነት እንዲንቀሳቀስ፣ በተለይ ጦርነቱ የተካሔደባቸው አካባቢዎች፣ በፈንጂ አምካኝ ባለሞያዎች በሚገባ ተፈትሸው የሚጸዱበት አስተማማኝ አሠራር በአፋጣኝ እንዲዘረጋ፣ጥሪ አቅርበዋል፡፡

XS
SM
MD
LG