በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን ተፋላሚ ጄኔራሎቹ በተወካዮቻቸው በኩል ለመደራደር ተስማሙ


ካርቱም፤ ሱዳን
ካርቱም፤ ሱዳን

800 ሺሕ ሰዎች ከአገር ሊሰደዱ ይችላሉ - ተመድ

በሱዳን እየተፋለሙ ያሉ ጄኔራሎች በወኪሎቻቸው በኩል ለመደራደር ተስማምተዋል በተባለበት ሁኔታም በካርቱም ውጊያቸውን ቀጥለዋል። ለሶስት ቀናት መደረግ የነበረበት ተኩስ ማቆምም ሳይከበር ቀርቷል።

በአገሪቱ የሚገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዑክ ቮልከር ፐርዝስ ለአሶስዬትድ ፕረስ እንዳሉት ምናልባትም በሳዑዲ አረቢያ ሊካሄድ የሚችለው ድርድር መጀመሪያ የሚያተኩረው አስተማማኝ የተኩስ አቁም በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ነው።

በሌላ በኩል የሱዳን ተቀናቃኝ ጄኔራሎች ፍልሚያቸውን በቀጠሉበት ሁኔታ 800 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት ሊሰደዱ እንደሚችሉ የመንግስታቱ ድርጅት አስጠንቅቋል።

ሮይተርስ ያገኘው የድሮን ቪዲዮ እንዳመለከተው የአየርና የከባድ መሣሪያን ድብደባን ተከትሎ፣ የካርቱም ሰማይ በጭስ ተሸፍኗል።

በሱዳን የተመድ የሰብዓዊ መብት አስተባባሪ አብዱ ዲየንግ እንዳስጠነቀቁት ከሁለት ሣምንታት በላይ የቆየው ግጭት ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋግሯል።

የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸ በሱዳን ላለው የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ በሚሰጥበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ከተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ እና ከሌሎች የረድኤት ድርጅት ተወካዮች ጋር ትናንት ስብሰባ ተቀምጠዋል። ሩቶ ለሱዳን ሰብዓዊ ዕርዳት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ ከካርቱም ዜጎቿን የማስወጣቱን ሥራ አጠናክራ፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ 700 የሚሆኑ አሜሪካውያንን ከካርቱም ወደ ፖርት ሱዳን አዘዋውራለች።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው 200 የሚሆኑ እና በአካባቢው አገራት የሚገኙ ባለሙያዎች አሜሪካውያኑን ከካርቱም ለማስወጣት በመሥራት ላይ ናቸው።

በሱዳን ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ከሁለት ሣምንት በላይ ሲካሄድ በቆየው ውጊያ፣ እስካለፈው ሣምንት ድረስ 530 ሰዎች ሲገደሉ 4 ሺሕ 500 ደግሞ ቆስለዋል ሲል የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል። 70 ሺሕ የሚሁኑ ሰውች መዲናዋን ካርቱምን ለቀው እንደወጡ ይነገራል።

XS
SM
MD
LG