በሱዳን ባለፈው ዓመት ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጦር ኃይሉ ጠቅላይ አዛዥ አብደልፋታህ አል ቡርሃን ማንሳታቸውን ገዢው ሉዐላዊ ምክር ቤት አስታወቀ።
ጀነራሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚሰርዝ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የገለጸው ምክር ቤቱ ዕርምጃው የተወሰደው "የሽግግሩ ወቅት የተረጋጋ እንዲሆን የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት እንዲደረግ አመቺ ሁኔታ ለመፈጠር ሲባል ነው" ብሏል።
ትናንት ዕሁድ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እና በአዋጁ መሰረት የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ በቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት መሆኑን ዜናው ጨምሮ አመልክቷል።
ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሁለት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ይህኑ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቱ ልዩ ተወካይ ቮልከር ፐርዝ ጥሪ አቅርበዋል።
ሱዳን መፈንቅለ መንግሥቱ ከተካሄደበት ጊዜ አንስቶ በህዝባዊ ተቃውሞ እየተናጠች ስትሆን የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱዋቸው የኃይል እርምጃዎች ቢያንስ አንድ መቶ ሰዎች እንደተገደሉ እና በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች እንደቆሰሉ አፍቃሪ ዲሞክራሲ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር ይናገራል። ብዙ መቶ ሰዎችም ታፍሰዋል።
የሱዳን ወታደራዊ አዛዦች በትናንቱ ውሳኔያቸው ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ የታገደው የአልጀዚራ ቴሌቭዢን የቀጥታ ሥርጭት እንዲቀጥል ፈቅደዋል።