ሞንኪ ፖክስ ወይም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ሱዳን ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ መታየቱን የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለሽታው የተጋለጠ አንድ የ16 ዓመት ተማሪ ባለፈው ሣምንት የተገኘው በግጭት በምትተራመሰው ዳርፉር ግዛት ውስጥ መሆኑን ሚኒስቴሩ ትናንት ገልፆ ‘ተይዘው ሊሆን ይችላል’ ተብለው የተጠረጠሩ 38 ሰዎች ተመርምረው ሁሉም ነፃ መሆናቸውን አመልክቷል።
“መዛመቱን ለመቆጣጠር” በሚል የጤና ባለሥልጣናት ከተማሪው ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች በመለየት ላይ መሆናቸው ተዘግቧል።
ለሽታው የዓለም አጣዳፊ ትኩረት ሊሰጥ እንደገባ ባለፈው ሣምንት ያስጠነቀቀው የዓለም የጤና ድርጅት የሚገኝበትን ሁኔታ “አሳሳቢ ደረጃ” ሲል መድቦታል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ እስከአሁን በ74 ሃገሮች ውስጥ 16 ሺህ ሰዎች ላይ መታየቱን የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከላት (ሲዲሲ) አስታውቋል።