በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት መሪዎች 6 ዲፕሎማቶችን አባረሩ


ጀኔራል አብዱፈልታ አል ቡርሃን
ጀኔራል አብዱፈልታ አል ቡርሃን

የሱዳን ወታደራዊ ጁንታ በዚህ ሳምንት ያደረገውን የመንግስት ግልበጣ በመቃወም የተናገሩ ቢያንስ ስድስት አምባሳደሮችን ከሥራና ኃላፊነታቸው ማበረሩን የመንግስት ቴሊቪዥን ዛሬ ሀሙስ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡

ቴሌቪዥን ጣቢያው፣ ጀኔራል አብዱፈልታ አል ቡርሃን በዩናይትድ ስቴትስ፣ አውሮፓ ህብረት ቻይና ኳታርና እና ፈረንሳይ እንዲሁም በጀኔቭ የተባበሩት መንግሥታት የሱዳን ተወካይ መልክተኛን ማባረራቸውን ገልጿል፡፡

በዚህ ሳምንት አንድ ላይ የተሰባሰቡ የሱዳን ዲፕሎማቶች ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ባላፈው ሰኞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክና ባለቤታቸው መታሰራቸውን፣ ጀኔራል አልቡርሃን የልዕልና ምክር ቤቱን በመበተን፣ በአገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን አውግዘዋል፡፡

አሁን “የቀደሞ” የተባሉት በተባበሩት መንግሥታት የሱዳን አምባሳደር ኑረዲን ሳቲ፣ የሱዳንን ወታደራዊ ጁንታን የማይቀበሉት መሆኑን ትናንት ረቡዕ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡

“በዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ውስጥ ከሚገኙ ጓደኞቼ እዚህ በዩናይትድ ስቴትስም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍል ከሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ጋር፣ ይህ መፈንቅለ መንግሥት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑን በአስቸኳይ እንዲቀለበስ እሰራለሁ” ብለዋል፡፡

አልቡርሃን ወታደራዊ ኃይሉ እኤአ በሀምሌ 2023 ከሚደረገው ምርጫ በኋላ ሥልጣኑን ለተመረጠው የሲቪል መንግሥት እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡

ወታደራዊ ክፍሉ የሲቪሉን የሽግግር መንግስት የገለበጠው የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስወገድ መሆኑንም መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በሱዳን በርካታ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችና ግለሰቦች እየታሰሩ መሆኑ ሲገለጽ ተቃውሞው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

የዓለም ባንክ ባወጣው መግለጫ ለሱዳን የሚሰጠውን የገንዘብ እርዳታ የገታ መሆኑን ሲገልጽ በሱዳን ያለውን ሁኔታ “በቅርበት እየተከታተልንና እየገገመን ስለሆነ ምንም ዓይነት አዲስ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ አቁመናል” ብሏል፡፡

የዩናትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለሱዳን እንዲሰጥ የተወሰነው የ700ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG