ጦርነት ባመሳት በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ተፋላሚዎች የፖሊስ ዋና ጽ/ቤትን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ውጊያ ቢያንስ 14 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን ተሟጋቾች ዛሬ ሰኞ አስታወቁ፡፡
ካለፈው ሚያዝያ አጋማሽ አንስቶ ከሱዳን መደበኛ የጦር ሰራዊት ጋር በመዋጋት ላይ የሚገኘው የፈጥኖ ደራሹ ጦር የፖሊስ ዋና መ/ቤቱን በመቆጣጠር በጦርነቱ ድል ማስመዝገቡን ትናንት እሁድ ረፋዱ ላይ አስታውቋል፡፡
የፈጥኖ ደራሹ ጦር ባወጣው መግለጫ “ዋና ጽ/ቤቱ በሙሉ ቁጥጥራችን ስር ነው... በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሸከርካሪዎችን፣ መሳሪያዎችና ጥይቶችንም ይዘናል” ብሏል፡፡
ታንኮችን፣ፒክ አፕ መኪናዎችን እና ፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችንም መያዙን መግለጫው ጨምሮ ገልጿል፡፡
ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ አንድ የቀድሞ ጦር መኮንን በሃምዳን ደጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሹ ጦር ስትራቴጂክ ይዞታዎችን ተቆጣጥሮ መቆየት ከቻለ “ካርቱምን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጦርነት ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡
በጦር ሠራዊቱ አዛዥ በአብደል ፋታህ አል አልቡርሃን እና የቀድሞ ምክትላቸው በነበሩት ደጋሎ መካከል በሚካሄደው የስልጣን ትግል በመላዋ ሱዳን ወደ 2 ሺ800 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል፡፡
ሁለቱም ወገኖች ወገኖች በውጊያው የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ስለማያስታውቁ አንዲሁም ከባዱ ውጊአይ በተካሄደባቸው በዳርፉር እና በዋና ከተማዋ ካርቱም በየመንገዱ የወዳደቁ አስከሬኖች ስላሉ አሃዙ ከተጠቀሰው በእጅጉ ከፍ ሊል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡