በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሱዳን


"በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል እና የአማራ ክልል መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ሸሽተው በሚቀጥሉት ቀናት 5000 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ድንበር ተሻግረው ሱዳን ይገባሉ እንጠብቃለን" ሲሉ አንድ የሱዳን ባለሥልጣን ዛሬ መናገራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡

ዘገባው አክሎም በዚሁ ሳምንት ውስጥ ሦስት ሽህ ኢትዮጵያውያን ድንበር ተሻግረው ሱዳን መግባታቸውን እና አጠቃላዩ በሀገሪቱ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ስድሳ ሽህ መቃረቡን አመልክቷል።

ውጊያው እየተባባሰ በመሆኑ በቀጣዮቹ አርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ አምስት ሽህ ጥገኝነት ጠያቂዎች ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን ሲሉ የሱዳን ከሰላ ክፍለ ግዛት ባለሥልጣን መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ የተነሳ ሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ወንዝ ሞልቶ በጎርፍ በመጥለቅለቁ ሊሻገሩ የሞከሩ ሦስት ኢትዮጵያውያን መስጠማቸው ባለሥልጣኑ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

በትግራይ ክልል ውጊያው ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሺዎች የተቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እና ከአራት መቶ ሺህ የሚበልጡ ለረሃብ መዳረጋችውን የተመድን ጠቅሶ ያወሳው ዘገባው በግዛት ይገባኛል ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት የትግራይ ክልል እና የአማራ ክልል የተጣመዱበት ጭቅጭቅ ባሁኑ ወቅት የግጭቱ ዋነኛ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን አመልክቷል።

ባለፈው አርብ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ ስላለው ሰብዓዊ ሁናቴ እጅግ በጣም ስጋት አድሮብናል፤ ከባድ የምግብ እና የሌላም አቅርቦት ችግር ተፈጥሯል ማለቱን ዘገባው አክሎ ለአራት ሚሊዮን በአጣዳፊ የምግብ ችግር ላይ ያሉ ሰዎች ያልተገደበ የሰብዓዊ ረድኤት ተደራሽነት ሊኖር እንደሚገባ ማሳሰቡን ዘገባው አውስቷል።

XS
SM
MD
LG