በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ ወታደሮች ጥቃት አድርሰውብኛል ስትል ሶማሊላንድ ከሰሰች


ራሷን ነጻ አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊላንድ ወታደሮቼን አጥቅታብኛለች ስትል ትናንት እሁድ ሶማሊያን ከሳለች።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአጨቃጫቂ ድንበር ላይ ከተደረገ ከባድ ውጊያ በኋላ የተኩስ አቁም ሥምምነት ላይ ቢደረስም፣ የሶማሊያው ወገን ወታደሮቼን አጥቅቷል ስትል ሶማሊላንድ ከሳለች።

በእአአ 1991 ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ዓለም አቀፍ እውቅና ባታገኝም፣ ሁከት በበዛበት ቀጠና ውስጥ የሰላምና መረጋጋት ተስፋ ተደርጋ ትቆጠራለች።

ባለፉት ጥቂት ወራት ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት እየተስተዋለባት ይገኛል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ሳምንት እንዳለው ‘ላስ አኖድ’ በተባለችው አጨቃጫቂ ከተማ በሶማሊላንድ ወታደሮችና ለሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ታማኝ በሆኑ ሚሊሺያዎች መካከል በተደረገ ውጊያ ቢያንስ 20 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ትናንት እሁድ ደግሞ በሶማሊላንድ መዲና የሚገኙ ባለሥልጣናት የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ወታደሮች በማለዳው የሶማሊላንድ ወታደራዊ ኃይሎችን አጥቅተዋል ብለዋል።

የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ እንዳመለከተው ባለሥልጣናቱ በጥቃቱ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ከመናገር ቢቆጠቡም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሞቃዲሹ ላይ ተጽዕኖ በማድረግ ወታደሮቿን ከሶማሊላንድ ድንበር እንድታስወጣ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ሞቃዲሹ በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር የለም።

‘ላስ አኖድ’ በተባለችውና በሶማሊላንድና በፑንትላንድ ይገባኛል ጥያቄ የሚቀርብባት የንግድ መተላለፊያ ከተማ ባለፈው ሰኞ ውጊያ ተደርጎ ነበር።

ውጊያው የጀመረው የአካባባኢው ሽማግሌዎች “ለሶማሊ ፌዴራል ሪፑብሊክ አንድነትና ሉአላዊነት” ያላቸውን ድጋፍ ከገለጹና ሶማሊላንድ ወታደሮቿን ከአካባቢው እንድታስወጣ ከገለጹ በኋላ ነበር።

በውጊያው ስንት ሰዎች እንደሞቱ የታወቀ ነገር የለም ብሏል ኤኤፍፒ በሪፖርቱ። የተመድ ግን በውጊያው ቢያንስ 20 ሰዎች እንደተገደሉ አስታውቆ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል። ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር በበኩሉ ባለፈው ቅዳሜ እንዳስታወቀው አንድ በጎ ፈቃደኛ አባሉ ተገድሏል።

XS
SM
MD
LG