በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊላንድ ውስጥ ሰልፈኞችና ፖሊስ ተጋጩ


ሶማሊላንድ
ሶማሊላንድ

በድጋሚ የታደሰ

ከሶማሊያ መገንጠሏልን በምትናገረው ሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ውስጥ ዛሬ ሐሙስ በተቃዋሚ ሰልፈኞችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ አንድ ሰው መገደሉንና ብዙ ሰው መጎዳቱን አንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን መሪ ገልፀዋል።

የግዛቲቱ መሪ ሙሴ ቢሂ አብዲን የሚቃወሙ መፈክሮች ያሰሙ በነበሩትና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መዘግየቱን በተቃዋሙ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸው ተነግሯል።

ሀርጌሳ የሚገኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን መሪ አህመድ ዩሱፍ ሁሴን ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ በሰጡት ቃል ተገድሏል ካሉት ዕድሜው ከሃያ ስምንት እስከ ሠላሳ ዐመት የሚሆን አንድ ሰው ሌላ ሦስት ሴቶች የሚገኙባቸው አሥራ አምስት ቁስለኞች ማየታቸውን ገልፀዋል።

“በተለይ ወጣቶቹ ወንዶችና ሴቶች ጎዳናዎችን አጥረው ስለነበረ ፖሊሶቹ ሊበትኗቸው የእውነት ጥይት ተኮሱባቸው" ብለዋል አህመድ ዩሱፍ።

ዩሲድ በሚል የእንግሊዝኛ ምኅፃር የሚጠራው የሶማሊላንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፈይሰል አሊ ዋራቤ "የፀጥታ ኃይሎቹ በሰላማዊ ሁኔታ በተሰለፉት ተቃዋሚዎች ላይ የጭካኔ ጥቃት አድርሰውባቸዋል" ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የእንደራሴዎቹ የውክልና ጊዜ ማብቃቱንና የፕሬዚዳንቱም የሥልጣን ዘመን የፊታችን ኅዳር እንደሚያበቃ የጠቆሙት ፈይሰል “አስተዳደሩ ምርጫ እንዲካሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሪፐብሊኳን መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ከትቷታል” ብለዋል።

እጅግ በከበደው ድርቅና በበረታው ግሽበት መሃል በተፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት “ሶማሊላንድ ከዚህ የከፋ ቀን አጋጥሟት አያውቅም” ሲሊ አክለዋል የተቃውሞው መሪ።

የአሜሪካ ድምፅ የሶማሊላንድ የማስታወቂያ ሚኒስትርንና የገዥውን የኩልሚዬ ፓርቲን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ሞቃዲሾ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሶማሊላንድ ገዢዎችና የተቃዋሚ መሪዎች ከሁከት ተቆጥበው ባስቸኳይ ወደ ፖለቲካ ንግግር እንዲገቡ መክሯል።

ኤምባሲው አያይዞም “ምርጫዎቹን በሚመለከት ወገኖቹ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ ሶማሊላንድ እስካሁን ባስመዘገበቻቸው የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ክንዋኔዎቿ ላይ አደጋ ይጋርጣል” ሲል አሳስቧል።

XS
SM
MD
LG