በመላው ዓለም የሚገኙ ሶማሊያውያን የሀገራቸውን ስድሳ ሁለተኛ የነጻነት በዓል በዛሬው ዕለት አክብረዋል። ሶማሊያ አሳሳቢ በሆነ በድርቅ፣ በምግብ ዕጥረት እና በዋጋ ግሽበት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በመሆኗ የዘንድሮው የነጻነት በዓል በጎላ ፈንጠዚያ እንዳልሆነ ተዘግቧል።
ላለፉት ከሠላሳ በላይ ዓመታት የሶማሊያ ህዝብ የነጻነት በዐሉን ሲያከብር የኖረው በሁከት መሃል ቢሆንም የዘንድሮው ዘንድሮውን ግን በከባድ ድርቅ ሳቢያ ከወዲሁ ቸነፈር ደረጃ ላይ የደረሰው ሁኔታ የተለየ ያደረገው መሆኑ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ ሰብዓዊ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ አብዱራህማን ዋርሳሜ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል በበርካታ ዓመታት ባልታየው የከበደ ድርቅ የተነሳ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለረሃብ አደጋ መጋለጡን ገልጸዋል።
አዲስ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መህሙድ ሞቃዲሾ ውስጥ ምጥን ተደርጎ በተዘጋጀ ሥነ ስራዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በዐሉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲከበር ከማድረግ የተቆጠብነው ወጪውን በመቀነስ ያለንን ውሱን ገንዘብ በድርቅ የተጎዱ ሰዎችን ህይወት ለማትረፍ ብናውለው ይሻላል በማለት ነው" ሲሉ አስረድተዋል።