በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ ማዕከላዊ ከተማ በፍንዳታ ተናጠች


የሶማሊያ ማዕከላዊ ከተማ በለደወይን
የሶማሊያ ማዕከላዊ ከተማ በለደወይን

የሶማሊያ ማዕከላዊ ከተማ የሆነችውን በለደወይን ዛሬ ከፍተኛ ፍንዳታ ንጧት እንደነበር ዓይን እማኞች ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለቪኦኤ እንደተናገሩት ሁለት በመኪና ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎች ላማጋላይ የተባለውን የአካባቢውን የመንግሥት አስተዳደር ቢሮ ኢላማ አድርገው እንደነበር ተናግረዋል። ፍንዳታውን ተከትሎ ከፍተኛ የሰው ጉዳት ሊኖር እንደሚችል በአካባቢው የሚገኙ ምንጮች ተናግረዋል።

ላማጋላይ የተባለው የአስተዳደር ማዕከል የሂራን ክልል አገረ ገዢን ጨምሮ፣ ሌሎች ባለሥልጣናት ቢሮ እንደያዘ ታውቋል።

በለደወይን ከሶማሊያ መዲና 337 ኪ.ሜ. ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ በቅርቡ የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለሥልጣናት ከሃገሪቱ ጦር ጋር በመተባበርና ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸውን መንደሮች ከአል-ሸባብ ቁጥጥር ነፃ አውጥተዋል።

የዛሬው ፍንዳታ የተከሰተው እንድ ከፍተኛ የአል-ሻባብ መሪ ሀራምካ በተሰኘ ቦታ ቅዳሜ ዕለት መገደሉን የሃገሪቱ መንግሥት እሁድ ማምሻውን ማሳወቁን ተከትሎ ነው።

የሀገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዳለው፣ ከአል-ሻባብ መሥራቾች አንዱ የሆነው አብዱላሂ ናዲር የተገደለው የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር በመተባበር ባደረገው የተቀናጀ ጥቃት ነው።

ናዲር ያለበትን ለጠቆመ 3 ሚሊዮን ዶላር እንደምትሸልም ዩናይትድ ስቴስት አስታውቃ ነበር። ሃራምካ የተባለውና የተገደለበት አካባቢ በአል-ሻባብ ቁጥጥር ሥር ያለ ሥፍራ ሲሆን፣ ዘመቻው የአየር ጥቃትን ያካተተ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል። በአል-ሻባብ ላይ የአየር ጥቃት ኣካሄደ እንደሆነ የሚናገረው በአፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ዕዝ እስከአሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

አል-ሻባባ የናዲርን ግድያ ወሬ በተመለከተ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።

XS
SM
MD
LG