በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሁለት ሩሲያውያን በአላስካ በኩል ገብተው አሜሪካ ጥገኝነት ጠየቁ


ሁለት ሩሲያውያን በአላስካ በኩል ገብተው አሜሪካ ጥገኝነት ጠየቁ
ሁለት ሩሲያውያን በአላስካ በኩል ገብተው አሜሪካ ጥገኝነት ጠየቁ

ከአስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ማምለጣቸውን የተናገሩ ሁለት ሩሲያውያን በትንሽ ጀልባ በመጓዝ ከአላስካ ግዛት ራቅ ብላ ከምትገኘው ደሴት ደርሰው እጃቸውን ለአሜሪካ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ሰጥተዋል።

የአላስካዋ ሴናተር ሊሳ መርኮውስኪ ቃል አቀባይ ካሪና ቦርገር ለአሶስየትድ ፕረስ እንደነገሩት፣ ቢሯቸው ከአሜሪካ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች እና ከጉምሩክና ድንበር ጠባቂው መሥሪያ ቤት ጋር ግኑኝነት በማድረግ ላይ ሲሆን፤ ሁለቱ የሩሲያ ዜጎች “ከግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ለማምለጥ ከሩሲያ የባህር ጠረፍ ላይ ከሚገኝ አካባቢ ተነስተው እንደመጡ” ተናግረዋል ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን ወታደራዊ ልምድና አገልግሎት ያላቸውን 300 ሺህ ሩሲያውያን ጦራቸውን ለማጎልበት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ካደረጉ ወዲህ በሺህ የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ሀገራቸውን ጥለው ሸሽተዋል። ጥሪው ወደፊት ሌሎችን ሊያጠቃልል ይችላል የሚል ፍራቻም አሳድሯል።

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መ/ቤት በበኩሉ፣ ሁለቱ ግለሰቦች አንከሬጅ ወደተባለው የአላስካ ከተማ ለምርመራ መወሰዳቸውንና፣ በሃገሪቱ የስደተኞች ህግ መሰረት እንደሚስተናገዱ አስታውቋል።

አርባ ሁለት የሚሆኑ ሩሲያውያን ባለፈው ነሃሴ በካናዳ በኩል ወደ አሜሪካ ሊገቡ ሞክረው፣ በድንበር ጠባቂዎች ተመልሰዋል። በዚህ መልክ ሊገቡ የሞከሩት ሩሲያውያን ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩ ታውቋል።

ሩሲያውያን በአመዛኙ ወደ አሜሪካ የሚገቡት ቪዛ በማይጠየቁበት በሜክሲኮ በኩል ነው። ወደ ሜክሲኮ ከተጓዙ በኋላ፣ ወደ አሜሪካ ድንበር በመምጣት ጥገኝነት ይጠይቃሉ።

XS
SM
MD
LG