በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን አንድ የአዕምሮ ህሙማን መታከሚያ ሆስፒታል በአየር ደበደቡ ሲሉ የግዛቲቱ አገረ ገዥ ከሰሱ


በሩሲያ ኃይሎች ጥቃት የፈራረሰ ሕንፃ ካርኪቭ፣ ዩክሬን እአአ መጋቢት 3/2022 ።
በሩሲያ ኃይሎች ጥቃት የፈራረሰ ሕንፃ ካርኪቭ፣ ዩክሬን እአአ መጋቢት 3/2022 ።

ዩክሬን የሩሲያ ኃይሎች በምስራቃዊ ግዛቷ ኢዚዩም የተባለች ከተማ የሚገኝ የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል ደብድበዋል ስትል ከሰሰች። የክፍለ ሃገሩ አገረ ገዢ ድርጊቱን "በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ አረመኒያዊ” ጥቃት ሲሉ ኮንነዋል።

የካርኪቭ ክፍለ ሀገር አገረ ገዢ ኦሌህ ሲንጉቦቭ ሲናገሩ ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ሆስፒታሉ ውስጥ ሦስት መቶ ታካሚዎች እንደነበሩ ገልጸዋል። አንዳንዶቹ በመንቀሳቀሻ ወንበር ላይ የነበሩ ወይም መንቀሳቀስ የማይችሉ እንደነበሩ የገለጹት ባለሥልጣኑ ከህሙማኑ መካከል ሰባ ሦስት የሚሆኑትን ማውጣት ተችሏል ብለዋል።

አጠቃላዩ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር እየተጠናቀረ መሆኑ ነው የገለጹት። ይህ በሀገራችንና በሲቪሉ ህዝብ ላይ የተፈጸመ የጦር ወንጀልና የዘር ማጥፋት ድርጊት ነው ብለዋል።

ሮይተርስ ይህንን ሩሲያ ዩክሬይንን ከወረረችበት ጊዜ ጀምሮ ከባድ ውጊያ በሚካሄድበት አካባቢ ተፈጽሟል የተባለውን አድራጎት ወዲያውኑ ለማረጋገጥ አልቻለም። ሩሲያ በበክሏ ዩክሬንን ትጥቅ ለማስፈታት እና ከናዚ ለማጽዳት የወሰድኩት ልዩ ኦፐሬሽን ባለችው ጥቃት ሲቪሎችን ዒላማ አላደረኩም በማለት ስታስተባብል ቆይታለች።

ከትናንት በስቲያ ረቡዕም ሩሲያ በደቡቧ የዩክሪይን ከተማ በማሪዮፖል ሆስፒታል ላይ የቦምብ ጥቃት አድርሳ ሦስት ሰዎች መግደሏን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ሩሲያ ደርሷል የተባለውን ጥቃት እመረምራለሁ ያለች ሲሆን አንዳንዶቹ ባለሥልጣናቷ ደግሞ "የሀሰት ወሬ" ብለውታል።

የክፍለ ሃገሩ አገረ ገዢ በተጨማሪም ሩሲያ በትልቋ የክፍለ ሃገሩ ከተማ በካርኺቭ በአንድ ቀን ውስጥ የመኖሪያ አካባቢዎችን ሰማኒያ ዘጠኝ ጊዜ በመድፍ ማጥቃቱዋን ገልጸው ሆኖም የኒዩክሊየር ላቦራቶሪ በሚገኝበት ተቋም ላይ ባደረሰችው ጥቃት በሲቪሎች የተደቀነ አደጋ እንደሌለ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG