በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቁጣና ሽልማት - የትናንት ኦስካር ምሽት


የጥበብ ሥራዎች ዘጠና አራተኛ አካደሚ ሽልማቶች እአአ መጋቢት 26/2022
የጥበብ ሥራዎች ዘጠና አራተኛ አካደሚ ሽልማቶች እአአ መጋቢት 26/2022

የጥበብ ሥራዎች ዘጠና አራተኛ አካደሚ ሽልማቶች ምሽት በደመቀ፤ ደግሞም ብዙዎችን ባስደነገጠና ባስገረመ አጋጣሚ ትናንት ምሽት ተከናውኗል። ሁለት ዐይን ያስፈጠጡ፣ አዕምሮን የናጡ አጋጣሚዎች በአንድ የኦስካር መድረክ!

ለሁለተኛነት የተጠበቀው “ኮዳ” (መስማት የተሳናቸው አዋቆች ልጅ) ፊልም “ምርጥ ፊልም” ተብሎ ባልተጠበቀ ሁኔታ ኦስካርን ሲጎናፀፍ፤ በሌላ በኩል ገናና፣ በብዙዎች ተወዳጁ ዊል ስሚዝ ከእርሱ ባልተናነሰ ሁኔታ የሚከበረውን የመድረክ ቧልተኛና ተዋናይ ክሪስ ሮክን መድረክ ላይ ወጥቶ በጥፊ አንድዶታል።

“ኦ! ዋው! ዋው! ዊል ስሚዝ’ኮ በጥፊ አ..ን አበላኝ!” አለ ክሪስ ባለማመን አስተያየት አፍጥጦ አሁን የተቃጠለ ፊቱን እያሻሸ።

ተዋናይ ዊል ስሚዝ የመድረኩ አስተናባሪ የነበረውን ኮሜዲያኑን ክሪስ ሮክን በጥፊ የመታበት ፎቶ
ተዋናይ ዊል ስሚዝ የመድረኩ አስተናባሪ የነበረውን ኮሜዲያኑን ክሪስ ሮክን በጥፊ የመታበት ፎቶ

የዊል ስሚዝ ሚስት ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ እራሷ ላይ ፀጉር የለም፤ ባሏ አጠገብ ተቀምጣለች።

የዛሬ 25 ዓመት ወጥቶ በነበረ ጂ.አይ. ጄን ፊልም ላይ ዋና ገፀ ባህርይ የነበረችው ጄን ባህር ኃይል ለመቀጠር ስትል ፀጉሯን ተላጭታ ነበር የቀረበችው። ፊልሙ “አድቬንቸር” የሚባል ብዙ አስደናቂና ልብ አንጠልጣይ ትዕይንቶች ያሉት ድራማ ነው።

እናም መድረኩ ላይ የነበረው ክሪስ ይቀልዳል፤ ዐይኖቹ ባጋጣሚ ጄዳ ላይ ያርፋሉ። “ጄዳ፤ እወድሻለሁ! ጂ.አይ. ጄን ሁለትን በጉጉት እጠብቃለሁ! እሺ?” ማለት! ባይልስ?!

ያኔ አጠገቧ ተቀምጦ ይስቅ የነበረው ዊል (ባሏ) ሚስቱ ዐይኖቿን እያጉረጠረጠች ባለመደሰት ስታንከባልል ያስተውላል። በቀጣዮቹ ሰከንዶች ውስጥ መድረኩ ላይ የታየው በኦስካር ታሪክ ተፈጥሮ አያውቅም።

ሥነ ሥርዓቱን በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ በቀጥታ ሲተላለፍ ይከታተሉ የነበሩ የአሜሪካ ተመልካቾች ያኔ የሆነውን ለማየት ዕድል አላገኙም፤ የሃገር ውስጥ ጣቢያዎች በሰከንዶች ውስጥ ከአየር ላይ ሰወሩት። ከአሜሪካ ውጭ ባሉ ቻነሎች ላይ ግን ያለከልካይና አጋጅ በዓለሙ ተናኝቷልና አጭሩ ታሪክ ወዲያው ያለም ወሬ ሆነ። አሜሪካዊያኑም የራሳቸውን ታሪክ ከውጭ አግኝተውት /ወስደውት/ ይኸው እንደትንግርት እየተቀባበሉት ነው። ወሬው ሳር ቅጠሉን ሞልቶታል።

ዊል ስሚዝ የሚስቱ ዐይኖችና ቀልቡ ያዘዙትን ከፈፀመ በኋላ ተመልሶ ተቀመጠና በብዙ መረን ቃላት አጀብ፣ በጩኸትና በቁጣ “ሁለተኛ የሚስቴን ስም እንዳታነሳ!” ብሎ አስጠነቀቀው።

በርግጥ በኋላ እራሱ ዊልም የቴኒስ ንግሥቶቹን ቪነስና ሴሬና ዊልያምስን አባት ታሪክ በያዘው “ኪንግ ሪቻርድ” ፊልም ውስጥ ስለነበረው ተውኔት የምሽቱ ተሸላሚ ነበርና ያንን ለመቀበል የወጣ ጊዜ ፊቱ በእንባው እንደራሰ

“አካዳሚውን ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብሏል። ክሪስን ግን አላለም። “ክሪስ ላይ የተፈፀመው አድራጎት አግባብ አይደለም፤ ዊል ሊከሰስ ይገባዋል” የሚሉ በጣም የተናደዱ ሰዎች አሉ። “የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ግን እንዲህ ተደረግኩ ብሎ በዊል ላይ ዶሴ የከፈተ ወይም አቤቱታ ያሰማ የለም” ብሏል። ክሪስ “የጁን ይስጠው!” ብሎ ትቶት ይሆን? ይህንን አልሰማንም። ቀኑን ግን “ታሪካዊ” ብሎታል፤ በርግማን ይሁን በግርምት ለጊዜው አይታወቅ እንጂ።

በነገራችን ላይ ጄድ ባደረባት አሎፔሺያ የሚባል የጤና መስተጓጎል ምክንያት ፀጉሮቿ እንደሚረግፉ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ተናግራ ነበር።

ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ቁጣና ሽልማት - የትናንት ኦስካር ምሽት
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:12 0:00

XS
SM
MD
LG