ናይጄሪያውያን፣ ፕሬዚዳንት ባይደን፣ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የመጀመሪያው ቀን፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስልምና እምነት ተከታዮች በሚበዙባቸው አገሮችና በአንዳንድ አፍሪካ አገሮች ላይ ጥለውት የነበረውን እገዳ በማንሳታቸው ተስፋቸው ማንሰራራቱን ተናግረዋል፡፡
ናይጄሪያ ትራምፕ ጥለው በነበረው የ2017ቱ እገዳ ከተጎዱ አገሮች አንዷ ነበረች፡፡
ለእገዳው የተሰጠውን ምክንያት “ለደህንነት ስጋት” የሚል ሲሆን፣ ተቺዎች ግን ጉዳዩን የተወሰነውን የህብረተስብ ክፍል ለማግለል እንደ ተላለፈ ውሳኔ አድርገው ወስደውታል፡፡
በቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካይነት ተጥለው በነበረው እገዳ ውስጥ ያልነበሩ፣ ሌሎች ስድስት አፍሪካ አገሮችም በተጨማሪነት ተካተው ነበር፡፡ ተችዎች የሙስሊም የአፍሪካ አገሮች እገዳ” ብለው ይጠሩታል፡፡ በእገዳው ውስጥ ተካተው ከነበሩት አገሮች መካከል፣ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማልያ ሶሪያ፣ የመን፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ናይጄሪያ ፣ማይናማር፣ ኤርትራ፣ ኪርግስታን፣ ሱዳን እና ታንዛያ ይገኙበታል፡፡
ከእነዚህ አገሮች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሚመጡ ወይም ወደ እነዚህ አገሮች ለሚሄዱ ተጓዦች በሚሰጠው ቪዛ ላይ የተጣሉ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ገደቦች ነበሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደን ሥልጣን በያዙ የመጀመሪያው ቀን ያደረጉት፣ የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ በማውጣት፣ በእነዚህ አገሮች ላይ የተጣለውን ገደብ ማንሳት ነበር፡፡
እገዳው ከሚመለከታቸው መካከል፣ በናይጄሪያ አቡጃ ነዋሪ ጆሴፍ አባ አንዱ ነው፡፡ እኤአ 2018 አዲስ ካገባት ባለቤቱ ጋር፣ የጫጉላ ሽርሽሩን በዩናትይድ ስቴትስ ለማድረግ አቅዶ ነበር፡፡ ለጉዞ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን አዘጋጅቶና መስፈርቶችንም አሟልቶ ቢያቀርብም ቪዛውን ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡
"ናይጄሪያ በፕሬዚዳንት ትራምፕ እገዳው ከተጣለባቸው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ አንዷ ስለነበረች በናይጄሪያ እና በአሜሪካ መካከል የሚደረግ ጉዞ ጨርሶ የሚቻል አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡" ብሏል ጆሴፍ፡፡
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ አፍሪካን በሚመለከት፣ በአንድ ወቅት የሰጡት አስተያየት፣ እጅግ የወረደ አስተያየት ሲሆን፣ ለእገዳው የሰጡት ምክንያት የደህንነት ስጋት ነው የሚል ነበር፡፡
ይህ እንደ ጆሴፍ አባ ባሉት ናይጄሪያውን ዘንድ፣ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የደህንነት ስጋት፣ ልክ እንደ ኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውና ሁሉንም አገሮች የሚመለከት እንጂ፣ ናይጄሪያን ብቻ የሚመለከት አይደለም ባይ ነበሩ፡፡
አሁን ባይበደን የተላለፈውን ውሳኔ ግን የጉዞ ወኪል ድርጅት ባለቤት የሆኑት ናይጄሪያዊው ቴዎ ቻርለስ እንዲህ ይገልጹታል
“እንደኔ ላሉ የቢዝነስ ሰዎች ይህ ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ በተለይም በጉዞ ኢንደስትሪ ውስጥ ያለ ሰው፣ በአሜሪካና በናይጄሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት በመጠቀም ብዙ እድሎች እየመጡ መሆኑንም መመልከት ይችላል፡፡”
ጆሴፍ አባ እንደሚለው ከአሁን በኋላ ናይጄሪያውን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመላለስ ይችላሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የንግድ ድርጅቶችም ገቢ ይጨምራል፡፡
(የቪኦኤ ዘጋቢ ቲሞቲ ኦቢዙ ከናይጄሪያ አቡጃ የላከውንና ሌሎችች ዘገባዎችን በማጣቀስ የቀረበ)
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡