በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከናይጄሪያ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ አውሮፓ ለመላክ ጥረት ተጀምሯል


የናይጄሪያ የፔትሮሊየም ሚኒስትር ቲሚፒሬ ሲልቫ
የናይጄሪያ የፔትሮሊየም ሚኒስትር ቲሚፒሬ ሲልቫ

የአውሮፓ ሀገሮች ከሩስያ የተፈጥሮ ሀብት አቅርቦት ለመላቀቅ እየሞከሩ ባሉበት ባሁኑ ወቅት አልጄሪያ ኒጀር እና እና ናይጄሪያ ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምረውት የነበረውን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጄክት እያንቀሳቀሱ ናቸው።

ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀው ይህ ትራንስ ሰሃራ ጋዝ ፓይፕላይን የተባለው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧምቧ ግንባታ ዕቅድ ነዳጅ ከናይጄሪያ በአልጄሪያ በኩል አድርጎ ወደአውሮፓ በየዓመቱ ሠላሳ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ማስተላለፍ የሚችል መሆኑ ተገልጿል።

የናይጄሪያ የፔትሮሊየም ሚኒስትር ቲሚፒሬ ሲልቫ ለግንባታው የሚያስፈልገው ወጪ ከአውሮፓ ይመጣል ነው ያሉት። ከወዲሁም ከአውሮፓ ኩባኒያዎች እና መንግሥታት ጋር ንግግር ጀምረናል ብለዋል።

የናይጄሪያ የአልጄሪያ እና የኒጀር የፔትሮሊየም ሚንስትሮች አቡጃ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ ዕቅዱን ለማንቀሳቀስ መወሰናቸው ተዘግቧል።

ዕቅዱን ዳር የማድረሱ ጉዳይ የመንግሥታትን ቁርጠኝነት ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች እንዳሉበት ጉዳዩን የሚከታተሉ ይናገራሉ።

ከአርባ ዓመታት በፊት የተወጠነውን ዕቅድ ለማንቀሳቀስ ያበረታታቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምታካሂደው ጦርነት የተነሳ የአውሮፓ ሀገሮች ከነዳጅ ንግድ ገቢ እንዳታገኝ ለማድረግ የያዙት ጥረት መሆኑ ተመልክቷል።

በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ልዑካን በዚሁ ጉዳይ ወደ አቡጃ ተጉዘው ውይይት አድርገው እንደነበር ዘገባው ጨምሮ አውስቷል።

XS
SM
MD
LG