ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ የባህር ኃይል አውዳሚ መርከቦችን ወደስፔይን እንደምትልክ እና ፖላንድ ለሚገኘው ለአምስተኛው የጦር ኃይል ሰራዊት ቋሚ ክፍለ ጦር እንደምታቋቁም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ።
ሮሜንያ ላይም 3000 ወታደሮች እና 2000 ሌሎች ሰራተኞች በፈረቃ እንደሚመደቡ እና ሁለት ተጨማሪ ኤፍ -35 ተዋጊ ጀቶች ወደብሪታንያ እንደሚላኩ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንቱ ስፔይን ማድሪድ ላይ ለተሰባሰቡት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገሮች መሪዎች ባደረጉት ንግግር፣
"ዩናይትድ ስቴትስ አውሮፓ ውስጥ ያላትን ቁመና እየተለዋወጠ ለሚገኘው የፀጥታ ሁኔታ ምላሽ ለመስጥት በሚያስችላት እና ለጋራ ጸጥታችን በሚጠቅም መንገድ እንደምታጠናክር አስታውቃለሁ" ብለዋል።
መሪዎቹ ለዩክሬን በሚሰጡት ድጋፍ እንዲሁም ኔቶ አሁን ያሉትን እና መጪ ፈተናዎችን እንዴት መጋፈጥ እንዳለበት ይነጋገራሉ።
ዩክሬን የሩሲያን ጥቃት መመከት የሚችላት ተጨማሪ ድጋፍ ለመስጠት ይስማማሉ ተብሎ ይጠበቃል። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ለጉባዔው በቪዲዮ ንግግር ያደርጋሉ።