በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ላቭሮቭ በአፍሪካ ጉብኝታቸው ምዕራቡን ዓለም ወቀሱ


የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ ከኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋራ
የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ ከኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋራ

በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በዓለም በተፈጠረው የምግብ ቀውስ ምክንያት መገለል የደረሰባት ሩሲያ፣ አጋሮችን ለማግኘት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሰርጌይ ላቭሮቭን ሰሞኑን ወደ አፍሪካ ልካለች።

የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ መዲና ሲያጠናቅቁ፣ “ለዓለም የምግብ እጥረት ቀውስ ተጠያቂው ምዕራብ ሃገራት የሚከተሉት ፖሊሲ ነው” በማለት ወቀሳ አቅርበዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፅመችውን ወረራ ካላወገዙት አብዛኛው የአፍሪካ ሃገራት አጋርነትን ትሻለች። ላቭሮቭ በአፍሪካ ጉብኝት ያደረጉት ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ዕርዳታ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም እንደምትለግስ ባስታወቀችበት ወቅት ነው።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በየሄዱባቸው የአፍሪካ ሃገራት ዋና ጉዳይ ሆኖ የተነሳው የሩሲያ እና የዩክሬን እህል ለገበያ የሚቀርብብትን ሁኔታ የተመለከተ ነው።

የኮንጎ ሪፐብሊክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ክላውድ ጋኮሶ ላቭሮቭን ከተቀበሉ በኋላ ፤ “ሰርጌይ ላቭሮቭን ስለምንቀበል ደስ ብሎናል። የመጡትም ከመልካም ዜና ጋር ነው።” ብለዋል።

አያይዘውም “በቱርክና በተባበሩት መንግሥታት መሪነት የተደረሰው ስምምነት፣ በጥቁር ባህር እና በቱርክ ወገን ባለው ባስፈረስ በተባለው የውሃ መተላለፊያ በኩል ከዩክሬን ስንዴ ለገበያ የሚቀርብበትን ሁኔታ የፈጥራል” ብለዋል።

ባለፈው የካቲት ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯና ወደቦቿን በመዝጋቷ ወደ ቀረው ዓለም ይላክ የነበረው እህል ታግቷል። በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር እህል ወደ ገበያ ሳይገባ በመቅረቱ የሸቀጥ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

የውጪ ጉዳይ ምኒስትሩ ላቭሮቭ ረቡዕ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ ግን፣ ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ በፊትም በኮቪድ 19 ምክንያት እና የምዕራቡ ዓለም “አረንጓዴ ፖሊሲ” ብሉ በሚከተለው ፖሊሲ ምክንያት የምግብ ዋጋ ጨምሮ እንደነበር ተናግረዋል።

“የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ነገሩን አዛብተው እንደሚያቀርቡ አውቃለሁ፤ ልክ ከየካቲት ወር በፊት ምንም የምግብ ችግር እንዳልነበር” ብለዋል ላቭሮቭ።

አንድ ባለሞያ ለቪኦኤ እንደተናገሩት ግን ላቭሮቭ በአፍሪካ ጉብኝታቸው በዓለም የተፈጠረው የምግብ ቀውስ በሩሲያ ወረራ ምክንያት ነው የሚለውን ትርክት ለመቀየር ጥረት አድርገዋል።

“ሩሲያ ከዩክሬን እህል ያልወጣበትን ምክንያትና በዓለም ላይ የደረሰውን የምግብ ቀውስ ከተጣለባት ማዕቀብ ጋር በሐሰት ማገናኘት ነው የምትፈልገው። እዚህ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ወደቦች የሚገኘውን እህል ማገዷና ሆን ብላ የዩክሬንን የግብርና ሥርዓት ማውደሟ የጉዳዩ ማጠንጠኛ ነው” ይላሉ በጦርነት ጥናት ተቋም ሩሲያዊ ተመራማሪ የሆኑት ናታሊያ ቡጋዮቫ።

ሌላው ተመራማሪ ደግሞ በወረራው ምክንያት አፍሪካ ይበልጥ ተጎጂ እንደሆነች ይናገራሉ።

“በእርግጥ በካባቢው የምግብ ደህንነት ያለመኖር የፈጠረው ጫና እየታየ ነው። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በአካባቢው በቅርቡ ተጉዘው የ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል” ብለዋል ሱዛን ስቲጋንት ከእሜሪካ የሰላም ተቋም።

ሱዛን ስቲጋንት ለቪኦኤ ጨምረው እንደተናገሩት ከዓለም 60 በመቶ የሚሆነው ያልታረሰ መሬት የሚገኘው አፍሪካ ነው። አህጉሪቱ ግን 40 በመቶ ለሚሆነው የእህል አቅርቦት ሩሲያ ላይ ጥገኛ ነች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው 47 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች ከባድ ረሃብ ገጥሟቸዋል። በተለይ አፍሪካ ዋናው ገፈት ቀማሽ ነች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩስያ ባለፈው ቅዳሜ የኦዴሳ ወደብን መደብደቧ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በቱርክ ኢስታንቡል ላይ የተደረገውን ስምምነት ችግር ላይ ጥለዋል ብለዋል። ዘለንስኪ እንዳሉት ሞስኮ ሁሌም ቃሏን ለማጠፍ መንገድ ትዘይዳለች።

የላቭሮቭ የአፍሪካ ጉብኝት ግብጽን፣ ዩጋንዳ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክንና ኢትዮጵያን ሲጨምር፤ በዩክሬን ጥቁር ባህር በኩል የእህል አቅርቦት እንደሚቀጥል ለየቀጠናው መሪዎች ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ላቭሮቭ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋራ የተገናኙ ሲሆን በኢኮኖሚ መስክ እንዲሁም አጠቃላይ ግንኙታቸውን ለማጠናከር ሁለቱ ወገኖች ተስማምተዋል ሲሉ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ላቭሮቭ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር ስለመገናኘታቸው የተገለጸ ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእይታ ከተሰወሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ከአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎች ጋር ስለመገናኘታቸውም የተባለ ነገር የለም።

የላቭሮቭ ጉብኝት ሩሲያን እና ኢትዮጵያን የተመለከተ የሁለትዮሽ ጉብኝት ነው ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎች ለቪኦኤ ተናግረዋል።

ላቭሮቭ ኢትዮጵያ በነበሩበት ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ መንግሥት ድርቅን መቋቋሚያ የሚውል የ488 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ድርቅ እና ግጭት 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የምግብ ዕርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚ ትሬሲ አን ጄኮብሰን እርዳታውን ባሳወቁበት ወቅት እንዳሉት በአካባቢው ያለው ወቅታዊ የከባቢ አየር ሁኔታ “እስከፊና ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአፍሪካ የአሜሪካ አዲስ ልዑክ የሆኑት ማይክ ሃመር በዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ጉዟቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ፣ ይህም የፌዴራል መንግስቱንና የትግራይ አማፂያንን ለማሸማገል አሜሪካ የምታደርገው ጥረት አካል ነው ተብሏል።

XS
SM
MD
LG