በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ንግግር


የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ

በድጋሚ የታረመ

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ ሐሙስ ከሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ጋር ካርቱም ላይ እንደሚነጋገሩ ተዘግቧል፡፡

ውይይታቸው በሩሲያ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሚሆን የሱዳን መንግሥት የዜና ማሰራጫ ሱና ዘግቧል፡፡

ውይይቱ ከሁለቱ ሀገሮች የጋራ ግንኙነት በተጨማሪ ደቡብ ሱዳንን፣ ቻድን እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን ጨምሮ በግጭቶች የተጎዱ የሱዳን አጎራባች ሀገሮችን በሚመለከትም እንደሚያተኩር የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ አልሳድክ አመልክተዋል፡፡ በዝርዝር አላብራሩም፡፡

ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጉብኝት ቀደም ብሎ የዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ሀገሮች ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ወደሱዳን ተጉዘው ከወታደራዊ መሪዎቹ እና ከአፍቃሪ ዲሞክራሲ ቡድኖች ጋር የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ሽግግር በሚመለከት ለሁለት ቀናት ተወያይተዋል፡፡

እአአ ባለፈው 2021 ጥቅምት ወር የተካሂደው መፈንቅለ መንግሥት የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ሽግግር በአጭር አስቀርቶታል፡፡

ባለፈው 2022 መጨረሻ የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ከዋናዎቹ አፍቃሪ ዲሞክራሲ ቡድኖች ጋር ሲቪላዊ አስተዳደር ስለሚመሰረትበት መንገድ ቅድመ ሥምምነት ያደረጉ ሲሆን የመጨረሻውን ስምምነት ለመቋጨት ስለሚቻልበት መንገድ በዓለም አቀፍ አካላት ሽምግልና ንግግሩ ቀጥሏል፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወደሱዳን ከማቅናታቸው አስቀድሞ ማሊን እና ሞሪታኒያን ጎብኝተዋል፡፡

ዓለም ዓይኑን በአፍሪካ ግዙፍ የተፈጥሮ ሐብት ላይ በይበልጥ እየጣለ ባለበት በዚህ ወቅት ሩስያም ከአህጉሪቱ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በመንቀሳቀስ ላይ ነች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ በዚህ በአዲሱ 2023 ብቻ ወደአፍሪካ ሲጓዙ ይህ ሁለተኛ ጊዜያቸው መሆኑ ነው፡፡

XS
SM
MD
LG