በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ ኮሪያ አዲስ ፕሬዚዳንት መረጠች፤ ሰሜን ኮሪያ አዲስ ጠብ ለማጫር መዘጋጀቷን ፍንጭ ሰጠች


ተመራጩ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዩን ሶክ-ዮል ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡ ወቅት ሴኡል፣ ደቡብ ኮሪያ እአአ መጋቢት 10/2022
ተመራጩ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዩን ሶክ-ዮል ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡ ወቅት ሴኡል፣ ደቡብ ኮሪያ እአአ መጋቢት 10/2022

ወግ አጥባቂው የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ አቃቤ ሕግ ባለሥልጣን ዩን ሶክ-ዮል የፊታችን ግንቦት የመሪነቱን መንበር ሲረከቡ ከሚጠብቋቸው የውጭ ፖሊሲ ፈተናዎች ከሁሉ የበረታው ምን መልክ እንደሚኖረው ከወዲሁ አስታዋሽ መልዕክት የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው ይፋ በተደረገ ሦስት ሰዓታት ውስጥ ደረሳቸው።

መንግሥታዊ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ከፍተኛ ውጥረት ይከስታል በተባለ እርምጃዋ ፒዮንግያን በቅርቡ ወታደራዊ የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ ማቀዷን የሚጠቁም ፍንጭ ሰጥታለች።

ሰሜን ኮሪያ የምታመጥቃት ሳተላይት "የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ወራሪ ሰራዊት እና በክልሉ ያሉት ሸሪኮቻቸው” ያለቻቸውን ወገኖች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች "እየሆነ ባለበት ቅጽበት” መረጃ ትሰጣለች” ሲል መንግሥታዊው የኮሪያ ማዕከላዊ የዜና አገልግሎት ጨምሮ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ግን የሰሜን ኮሪያን አዲስ ሳተላይት የማምጠቅ ዕቅድ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች ከተከለከለ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ሙከራ እቅድ ጋር አዛምደውታል።

በሌላ በኩል ከሰሜን ኮሪያ አቅራቢያ የሚያደርገውን የደህንነት ክትትል ጥረት የሚያጠናክር መሆኑን እና እንዲሁም በአካባቢው ያሉት የቦላስቲክ ሚሳኤል መከላከያ ኃይሎች ዝግጁነት እየጨመረ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይል በትናንትው ዕለት ይፋ አድርጓል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በመደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ሲናገሩ፡ “የሚያሳስቡንን ጉዳዮች ምንነት ግልጽ አድርገናል። የምንወስዳቸውም እርምጃዎች በዋናነት ለእነኚህ ስጋቶች ትኩረት ለመስጠት ነው።” ብለዋል።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የወጣ አንድ የግምገማ ሪፖርት እንደጠቆመው፣ የዩናይትድ ስቴትስ የመረጃ ባለሥልጣናት ሰሜን ኮሪያ በያዝነው የአውሮፓውያኑ 2022 መገባደጂያ ግድም አህጉር አቋራጭ የቦለስቲክ ሚሳይል ልታስወነጭፍ ትችላለች አለያም የኒዩክሌር ሙከራ ታካሂድ ይሆናል” ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

አዲሶቹ ሃሳቦቿ የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም እና የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትሱ አቻቸው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2017 አንስቶ ተከታታይ ውይይቶችን ከማድረጋቸው አስቀድሞ ወደነበረው ውጥረት የሚመልሱ እርምጃዎች ተደርገው ተወስደዋል። የሁለቱ መሪዎች ውይይቶች እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2019 መፋረሱን ተከትሎም ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዋን አጠናክራ መግፋቷ ይታወቃል።

XS
SM
MD
LG