በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኦዲንጋ “ግዙፉ ሰኞ” በሚል የጠሩትን የዛሬ የብዙኀን ሰልፍ ሠረዙ


የኬንያው ተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ
የኬንያው ተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ

የኬንያው ተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ፣ በየሳምንቱ ሲደረግ የነበረውንና “ግዙፉ ሰኞ” በማለት ለዛሬ የቀጠሩትን የብዙኀን ተቃውሞ ሰልፍ በመሠረዝ፣ ከመንግሥት ጋራ ለውይይት ለመቀመጥ መወሰናቸውን ትላንት አስታውቀዋል፡፡

“ያለፈውን ዓመት ምርጫ አጭበርብረዋል፤” በማለት የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን የሚከሡት ኦዲንጋ፣ ደጋፊዎቻቸው በሳምንት ኹለት ጊዜ ለተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጡ ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በዛሬው ሰኞ ደግሞ፣ ብዙኀን የሚሳተፉበት ግዙፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግና ደጋፊዎቻቸው አገራቸውን መልሰው እንዲቆጣጠሩ ጥሪ አድርገው ነበር፡፡

ኾኖም፣ ሰልፉ አንድ ቀን ሲቀረው መሠረዙን በትላንትናው ዕለት ያስታወቁት ኦዲንጋ፣ ከኹለቱ ፓርቲዎች የተውጣጣ የፓርላማ ኮሚቴ፣ የምርጫ ሒደቱን በተመለከተ የቀረበውን ቅሬታ ለመመልከት በመሥራት ላይ መኾኑን አመልክተዋል፡፡ ምርመራው ውጤት የማያመጣ ከኾነ፣ ሰልፉን መልሰው የመጥራት፣ የመሰብሰብ እና የመቃወም መብታቸውን አጽንተው እንደሚቀጠሉበት አስጠንቅቀዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሩቶ ቀደም ብለው፣ ኦዲንጋ ሰልፉን እንዲሠርዙና ከፓርላማው ጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፈው ነበር፡፡

ባለፉት ኹለት ሳምንታት በተካሔዱት ሁከት የተቀላቀለባቸው ሰልፎች፣ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ የንግድ ሱቆችም ለዝርፊያ ተጋልጠዋል፡፡

የኬንያ አጋሮች እና ጎረቤት አገሮች፣ ሁከት በበዛበት ቀጣና፣ የጠና እና የረጋ ዴሞክራሲያዊት ተደርጋ የምትታየው አገር ሰሞናዊ ኹኔታ አሳስቧቸዋል፤ ተብሏል፡፡

XS
SM
MD
LG