የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የፍትህ ሥርዓቱን ለማሻሻል ያወጡት ዕቅድ እንዲሰርዙ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አይዛክ ሂርዞግ ተማጸኑ፡፡ ትልቁ የሀገሪቱ የሠራተኛ ማኅበርም ዕቅዱን በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ አካሂዷል፡፡
በትዊተር ገጻቸው ባወጡት ቃል “ የእስራኤል ጸጥታ፡ ኢኮኖሚ እና ኅበረተሰቡ ላይ አደጋ ተደቅኗል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “መንግሥት ዕቅዱን የሚመለከተውን ምክር ቤታዊ ሂደት ባስቸኳይ እንዲያቆም የምማጸነው ለአገራችን አንድነት በማሰብ ነው” ብለዋል፡፡
አስከትለውም ፕሬዚዳንቱ “ይህ ወቅት ኃላፊነት የተመላበት አመራር የሚጠይቅ በመሆኑ በምክር ቤቱ የገዢው ጥምረት እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ከሁሉም በላይ ለእስራል ህዝብ የሚበጀውን እንዲያስቀድሙ” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሠራተኛ ማኅበሩ በተጨማሪ ዋናው የሀገሪቱ የሀኪሞች ማህበር የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ዕቅዱን በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ ጠርቷል፡፡ በዋናው የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያም ወደውጭ የሚደረጉ በረራዎች ቆመዋል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የመከላከያ ሚኒስትር ማባረራቸውን በመቃወም በሀገሪቱ ዙሪያ በብዙ አስር ሺዎች የተቆጠሩ ሰልፎች አካሂደዋል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት በመንግሥቱ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ ዕቅድ ላይ ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ “ከዕቅዱ በተያያዘ የተፈጠረው ክፍፍል ወደጦር ኃይሉ እና የደህንነት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ እየዘለቀ በመሆኑ በሀገሪቱ ጸጥታ ላይ ሥጋት ደቅኗል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የብሄራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ኤድሪያን ዋትሰን ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ ትናንት ባወጡት መግለጫ “የእስራኤል መሪዎች ባፋጣኝ ሥምምነት ላይ እንዲደርሱ አጥብቀን መማጸናችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡