ኢራን በሥነ ምግባር ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ውላ ህይወቷ በጠፋው የ22 ዓመቷ ማሳ አሚኒ ሞት ምክንያት የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማቆም የምታደርገውን ዘመቻ ኩርዶች በሚኖሩበት የአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ዛሬ ማክሰኞ አጠናክራ ቀጥላለች ሲሉ አክቲቪስቶች ገለጹ፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የዋይት ሀውስ የደህንነት አማካሪ በማሳ አሚኒ ሞት የተቆጡ ተቃዋሚዎቹን ኢላማ ያደረገውን ጥቃት ቢያወግዙም፣ አመጽ በታኝ ፖሊሶች ግን ቢያንስ በኢራን ኩርዶች ክፍለ ግዛት ኩርዲስታን ዋና ከተማ ሳናንዳጅ ውስጥ በምትገኝ አንድ አካባቢ ላይ መተኮሳቸው ተነገሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የነዳጅ ዘይት ሠራተኞችም በሁለት ቁልፍ የነዳጅ ድፍድፍ ማጣሪያ ተቋማት ውስጥ ትናንት ሰኞ ተቃዋሚዎቹን በመቀላቀል ለመጀመሪያ ጊዜ ቁልፉን ኢንደስትሪ ከኢራን አገዛዝና አመጽ ጋር ማገናኘታቸው ተመልክቷል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢራን ፀጥታ ኃይሎች “ጠመንጃዎችንና አስለቃሽ ጋዞችን ያለምንም ልዩነት በሰዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ ሳይቀር ይጠቀማሉ” ሲል ከሷል፡፡
የሚሰራውንም ወንጀል ለመደበቅ፣ ኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ አውታሮችን ማቋረጧን የቀጠለችው ኢራን፣ ተቃዋሚዎቹ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም ዓለም ግፊት ሊያያደርግባት ይገባል ሲልም አምነስቲ አሳስቧል፡፡
ኢራን ዛሬ በተቃዋሚዎች ላይ ደርሷል ስለተባለው ጥቃት ምንም አስተያየት አልሰጠችም፡፡
ይሁን እንጂ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቃዋሚዎች ላይ ተወስዷል በተባለው እምርጃ የሥነ ምግባር ጠባቂ ፖሊሶችና የደህንነት ባለሥልጣናት ላይ እንግሊዝ በጣለቸው ማዕቀብ ማብራሪያ እንዲሰጡ በኢራን የኢንግሊዝ አምባሳደርን መጥራቱን አስታውቋል፡፡