በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢራን አስተያየት ላይ የአሜሪካ መልስ እየተጠበቀ ነው


 ፎቶ ፋይል፦ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኔ ምስል ፊት ለፊት በቴህራን፣ ኢራን በባሃረስታን አደባባይ ለዕይታ የቀረበ
ፎቶ ፋይል፦ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኔ ምስል ፊት ለፊት በቴህራን፣ ኢራን በባሃረስታን አደባባይ ለዕይታ የቀረበ

ኢራን የኑክሌር ሥምምነቱን እንደገና ለማነሳሳት በወጣው ሰነድ ላይ የሰጠችውን አስተያየት በተመለከተ አሜሪካ በቅርቡ መልስ ትሰጣለች ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን የቪኦኤው ክሪስ ሃናስ ዘገባ አመልክቷል።

በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቅብ እንዲላላ በምትኩም ኢራን ኑክሌር ማበልጸጓን እንድትቀንስ የተደረሰው ዓለም አቀፍ ሥምምነት ጋሬጣ ከገጠመው ዓመታት ተቆጥረዋል።

ከወራት ድርድር በኋላ በአውሮፓ ህብረት የወጣውን ሰነድ አሜሪካ በማጥናት ላይ ነች።

አንድ የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ሁለቱ ወገኖች ከሁለት ሳምንት በፊት ከነበሩበት የታሻለ ወደ ሥምምነት የቀረቡ ቢሆንም “አንዳንድ ክፍተቶች ግን ይቀራሉ” ማለታቸውን ክሪስ ሃናስ ዘገባ ጠቁሟል።

በአውሮፓ ህብረት የወጣው ሰነድ “የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ ከአሸባሪ ዝርዝር ውስጥ ይውጣ” የሚለውንም ሆነ “ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ፣ በሦስት ቦታዎች ላይ በታዩት የዩራኒየም ዱካዎች ላይ የሚያደርገውን ምርመራን እንዲያቆም” የሚሉትን የኢራን ጥያቄዎች እንዳልጨመረ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ተወካዮች ቪየና ውስጥ “በስማ በለው” እየተደራደሩ መሆኑ ታውቋል።

ሰይድ ሞሃመድ ማራንዲ የተባሉና የኢራን ተደራዳሪዎች አማካሪ በትዊተራቸው እንዳስታወቁት ግን ኢራን፤ እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ ከአሸባሪ ዝርዝር ውስጥ ይውጣልኝ ብላ ጠይቃ አታውቅም። እክለውም እንዳሉት ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ “የሃሰት ክሶቹን ፋይል ከመዝጋቱ” በፊት ኢራን ወደ ሥምምነቱን አትቀበልም።

ኢራን በአንድ ወገንና፤ አሜሪካ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ጀርመን በሌላ ወገን እአአ በ2015 “የኢራን ኑክሌር ሥምምነት” የተባለንና ሃገሪቱ ላይ የተጫነው ማዕቀብ እንዲላላ፣ ኑክሌር እንዳታበለጽግ የሚያግደውን ሥምምነት ለመፈጸም ተስማምተው ነበር።

እአአ በ2018 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ “ሥምምነቱ ለኢራን በጣም ያጋደለ ነው” በሚል ከሥምምነቱ ሲወጡ፣ ኢራን ደግሞ ሥምምነቱን በሚጥስ ሁኔታ ተጨማሪ ዩራኒየም በማበልጸግና የተሻሻሉ የኑክሌር መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ተጠምዳ ሰንብታለች።

XS
SM
MD
LG