የተዳከመውን የኒውክሊየር መርሃ ግብሯን የሚመለከተውን ውል ለማንሰራራት ቪየና ላይ ሲካሄድ በቆየው ንግግር በተቻለ ፍጥነት አዲስ ስብሰባ እንዲጠራ ኢራን ጠይቃለች። ኢራን ከብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ጀርመን እና ሩስያ ጋር በቀጥታ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ደግሞ በተዘዋዋሪ ስትነጋገር መቆየቷ ይታወሳል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሳኢድ ኻቲብዛዴህ ሀገራቸው ከሳውዲ አረቢያ ጋር ስላደረገቸው ውይይት ሲያስረዱ መጪውን ጊዜ ከወዲሁ ያጤነ እንደነበር ጠቅሰዋል።
"አዎንታዊ ውይይት ነበር። በታሰቡት ማቀፎች ዙሪያ በደምብ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት ተደርጓል። በከፍተኛ የፖለቲካ ባለሥልጣናት ደረጃ ውይይት ቢደረግበት በተለያዩ ዘርፎች ፈጣን ርምጃ ለማስመዝገብ ይችላል ብለን እንገምታለን።" ብለዋል።
እአአ በ2015 የተፈረመው የኢራን ኒውክሊየር ጉዳይ ስምምነት ቴህራን የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ የመስራት እንቅስቃሴ እንድታቆም በዚያ ልዋጭም ማዕቀቦች እንዲሰረዙላት ሲሆን ኢራን ያለማቋረጥ የጦር መሳሪያውን የመስራት ፍላጎት የለኝም ስትል ቆይታለች።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዩናይትድ ስቴትስን ከውሉ ማስወጣታቸው እና በቴህራን ላይ ከባድ ማዕቀቦችን መልሰው እንደጣሉባት እና ይህንኑ ተከትሎም ኢራን በውሉ የገባቻቸው ቃሎች ማጠፍ እንደጀመረች ይታወሳል።
ከአንድ ዓመት በፊት ቪየና ላይ የተጀመረው ንግግር ዩናይትድ ስቴትስ ወደውሥምምነቱ በመመለስ ማዕቀቦቹን እንድታነሳ እና ኢራንም በውሉ የገባችውን ቃል እንድታከብር ለማድረግ የታለመ ነው።