በድጋሚ የታደሰ
ፍልሰተኞችን የያዙ ሁለት ጀልባዎች ሰምጠው ቢያንስ 15 ሰዎች እንደሞቱ የግሪክ ባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ዛሬ አስታውቀዋል።
በተለያዩ አደጋዎች ከሰመጡት ጀልባዎች፣ አንዱ 40 ፍልሰተኞችን የያዘ ሲሆን፣ ሌስቦስ በተባለችውና ከቱርክ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት አጠገብ ሰምጧል ሲሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በዚህ አደጋ አስራ አምስት አስከሬኖች ሲወጡ፣ አምስቱን ሰዎች ግን ከሞት መታደግ ተችሏል። የተቀሩትን ፍለጋ እንደቀጠለ ነው።
ኪቲራ ከተባለቸው ደሴት አጠገብ በደረሰው በሌላው ሁለተኛ አደጋ 30 ፍልሰተኞችን ማትረፍ ተችሏል። ጀልባዋ የሰመጠችው ከትልቅ ቋጥኝ ጋር ከተጋጨች በኋላ ነው ተብሏል።
ሁለቱም ጀልባዎች በሰዓት እስከ 100 ኪ ሜ ፍጥነት ከሚነጉደው ነፋስ ጋር እየታገሉ በመቅዘፍ ላይ ነበሩ ሲሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ፍልሰተኞች ግሪክ ለመድረስ በቱርክ በኩል ያቋርጣሉ። ህገወጥ አስተላላፊዎች ግን ኤጂያን ባህር ላይ ካለው ቁጥጥር ለማምለጥ አደገኛ የሆኑ መሥመሮችን ይጠቀማሉ።