በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዌል ማክሮን በድጋሚ ተመረጡ


የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዌል ማክሮን
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዌል ማክሮን

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዌል ማክሮን ትናንት ዕሁድ በተካሄደው አገር አቀፍ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ተፎካካሪያቸውን ቀኝ አክራሪዋን ማሪን ለ ፔንን አሸንፈዋቸዋል።

ማክሮን ሃምሳ ስምንት ነጥብ አምስት ከመቶውን ድምፅ ሲያገኙ ለፔን አርባ አንድ ነጥብ አምስት ከመቶ አግኝተዋል። ሁለቱ ያገኙት ድምፅ እአአ በ2017 መጀመሪያ በተወዳደሩት ጊዜ ካገኙት ድምፅ ጋር ሲነጻጸር በይበልጥ የተቀራረበ መሆኑ ተመልክቷል።

እአአ በ2002 ፕሬዚዳንት የነበሩት ዣክ ሺራክ የ ለ ፔንን አባት አሸንፈው ለሁለተኛ ጊዜ መመረጣቸው ሲታወስ ከዚያ ወዲህ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ሥልጣን ላይ ያለ ፕሬዚዳንት ለሁለተኛ ጊዜ ሲመረጥ ማክሮን የመጀመሪያ ናቸው።

በርካታ መራጮች እጅግ ቀኝ አክራሪ የሆኑት ለ ፔን እንዳያሸንፉ ብለው ድምፃቸውን እንደሰጧቸው እንደሚገነዘቡ የገለጹት ማክሮን ለፈረንሳይን ህዝብ አንድነት እሰራለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።

"ድምፅ ለመስጠት ያልፈለጉትን ወገኖቻችንንም አስባቸዋለሁ። ዝምታቸው አንዳችንንም ለመምረጥ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የሚያሳይ በመሆኑ ለእነርሱም ምላሽ መስጠት ይኖርብናል። በመጨረሻም ማዳም ለ ፔንን የመረጣችሁ እንዳዘናችሁ ይገባኛል። ብለዋል።

ደጋፊዎቻቸው በደስታ ሆታ ሲያሰሙም ማክሮን "ተዉ! እኔ አሁን የፓርቲ ዕጩ አይደለሁም የፈረንሳዮች በሙሉ ፕሬዚዳንት ነኝ።" ብለዋል።

ማሪን ለ ፔን ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው ሲሸነፉ ይህ ሦስተኛቸው ነው። ይሁን እንጂ ባሁኑ ውድድር ከቀደሙት የተሻለ የመራጭ ድጋፍ አግኝተዋል።

በዚህኛው ፉክክር ለ ፔን የቀረቡት ለኑሮ ውድነት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ሙስሊም ሴቶች በአደባባይ በሂጃብ እንዳሸፋፈኑ መታገድ አለበት ከሚለው አቋማቸው በማፈግፈግ አክራሪ ገጽታቸውን ረገብ አድርገው ነበር።

ለ ፔን በኢማኑዌል ማክሮን መሸነፋቸውን በመቀበል ባሰሙት ንግግር ያገኙትን ድጋፍ ከድል እንደሚቆጥሩት አመላክተዋል።

"ከምንጊዜውም ይበልጥ ቁርጠኞች ሆነናል። ለፈረንሳዮች ለመቆም ያለን ፍላጎት ይበልጡን ጠንክሯል። ዛሬ ምንም ሀዘን አይሰማኝም፥ ቂምም አልይዝም። ሺ ጊዜ ተቀብረናል፥ ግን ጠፉ አለቀላቸው ያሉንን ታሪክ ሺ ጊዜ ምኞታቸውን ፉርሽ አድርጎባቸዋል።" ብለዋል።

ለ ፔን አስከትለውም ይህ የምርጫ ውጤት ለፈረንሳይ እና ለአውሮፓ መሪዎች የፈረንሳይ ህዝብ እንደማይቀበላቸው እና ለውጥ እንደሚፈልግ የሚያሳይ በመሆኑ ቸል ሊሉት አይችሉም ብለዋል።

ኢማኑዌል ማክሮን እና ማሪን ለ ፔን ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት ብቸኛው ክርክራቸው በአገር ውስጥ እና የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች እጅግ የተለያዩ አቋሞችን ይዘው ተከራክረዋል። ለ ፔን የታዳሽ የኃይል ምንጭ ዕቅዶችን ለማገድ እና ፈረንሳይ እንደ የአውሮፓ ህብረት እና የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በመሳሰሉት ተቋማት ተሳትፎዋ እንዲቀንስ ይፈልጋሉ።

የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዘሌንስኪ ዛሬ ንጋቱ ላይ በትዊተር ገጻቸው የልብ ወዳጅ ሲሉ ለጠሯቸውለኢማኑዌል ማክሮን የእንኳን ደስ ያለዎ መግለጫ አስተላልፈዋል።

ሩስያ ዩክሬይንን በመውረሯ በማዕቀቦች ለመቅጣት በተደረገው ዐለም አቀፍ እንቅስቃሴ ፈረንሳይ የመሪነት ሚና የተጫወተች እና ለዩክሬይን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረጓም ጭምር በርካታ የአውሮፓ መሪዎች በማክሮን በድጋሚ መመረጥ ደስታቸውን እየገለጹ ናቸው።

XS
SM
MD
LG