ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል እንድትሆን መፍቀዳቸውን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳኡሊ ኒልኒስቶ እና ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሳና ማሪን ገለጹ፡፡ ይህም ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ፊንላንድ ያደረገችውን አብይ የፖሊሊ ለውጥ ዳር ያደርሰዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሯ ባወጡት የጋራ መግለጫ የኔቶ አባል መሆናችን የሀገራችንን ጸጥታ ያጠናክራል በኛ መግባትም የጋራ መከላከያው ይጠናከራል ብለዋል፡፡ ቶሎ ብለን ማመልከቻውን ማስገባት አለብን ይህን ለማድረግ ከሀገራችን በኩል የሚያስፈልገው እርምጃ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ አንደሚጠናቀቅ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ አክለዋል፡፡
የፊንላንድ ፓርላማ እና ህዝቡ ጉዳዩን እንዲያስብበት እንዲሁም ከኔቶ እና ከስዊድን ጋር ለመነጋገር ጊዜ ከሰጡ በኋላ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን መሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
የስዊድን ባለሥልጣናትም የጋራ መከላከያውን ለመቀላቀል ማመልከቻ የማስገባቱን ጉዳይ በቅርቡ ትንቀሳቀስበታለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኔቶ ዋና ጸኃፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ ዛሬ በሰጡት ቃል ፊንላንድ የአእባልነት ማመልከቻ ካቀረበች የሞቀ አቀባበል እናደርግላታለን፣ ሂደቱም ባፋጣኝ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
ሩሲያ የኔቶን መስፋፋት እንደማትቀበል፣ ፊንላንድ እና ስዊድን ከገቡ ከባድ ወታደራዊ አና ፖለቲካዊ መዘዝ ይከተላል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በፊንላንድ እርምጃ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጦርነቱን በሚመለከተው ዜና ትናንት ዩክሬን ሩሲያ ወደአውሮፓ ሀገሮች መኖሪያ ቤቶች እና ኢንዱስትሪዎች የተፈጥሮ ጋዝ የምትልክበትን ቧንቧ ቆርጣባታለች፡፡
የሩሲያ ወታደሮች የተቆጣጣሯትን ኼርሰን ክፍለ ግዛት ክሬምሊን ወደግዛታችን መጠቅለል አለበት ሲሉ ሞስኮ ደቡባዊ ዩክሬን ውስጥ ያስቀመጠቻቸው አንድ ባለሥልጣን ተናገሩ፡፡
ወደምዕራብ አውሮፓ ከሚሄደው የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የሚያልፈው በዩክሬን በኩል መሆኑ ተገልጻል፡፡
የአውሮፓ ህበረት ሩስያ ዩክሬንን በመውረሯ፣ ለመቅጣት በተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦቷ ላይ መተማመኑን የሚቀንስበት መንገድ በመፈለግ ላይ መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡