ዋሽንግተን ዲሲ —
በግዙፍ የማህበራዊ ሚዲያ መድረክነቱ የሚታወቀው ፌስቡክ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ የድርጅት መጠሪያ ስሙን “ሜታ”ወደ ሚል መቀየሩን አስታውቋል፡፡
አሁን ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች “ባሻገር” ወደ ላቀ ቴክኖሎጂ በመሸጋገር ለእውነታውና ገሀዱ ዓለም እጅግየተቃረቡ በሚመስሉ የምስል እይታዎች (ቨርችዋል ሪያሊቲ) ተጠቃሚዎቹን ለማገልግል መዘጋጅቱን አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ትናንት በሰጡት መግለጫ “ሜታ የሚለው ቃል ከግሪክ የተገኘ ቃል መሆኑን” ገልጸው ትርጉሙም “ባሻገር” ማለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፌስቡክ፣ ኢነስታግራም፣ ዋትስ አፕና ሚሴንጀር አሁንም በዚያው ስምና አገልግሎታቸው ሜታ በሚለው ድርጅት ስር ይቀጥላሉ፡፡
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ድርጅት፣ በውስጥ ሠራተኞቹ ሳይቀር፣ “ወደ ጥላቻንግግሮችና የተዛቡ መረጃዎች መተላለፊያ መድረክነት እያመራ ያለ፣ ቸልተኛ ድርጅት መሆኑን እየተነሳ ሲተች መሰንበቱ ይታወሳል፡፡