ሱዳን የሚገኙ ከአምስት መቶ በላይ በጦርነት የተጎዳችው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች ወደኢትዮጵያ ለመመለስ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል። ሰላም አስከባሪዎቹ ለደህንነታቸው እንፈራለን፣ ብሄርን መሰረት ያደረገው ክፍፍል እየተባባሰ ነው በማለት ሱዳን የፖለቲካ ጥገኝነት እንድትሰጣቸው መጠየቃቸውን አዥንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
አራት ሺህ ወታደሮች ባሉት በሱዳን አቢዬ በተመደበው የመንግሥታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ እስካለፈው ዓመት ድረስ የሚበዛውን ቁጥር የያዙት የኢትዮጵያ ወታደሮች ነበሩ። ሆኖም የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት የግዛት ይገባኛል ጭቅጭቅ ከተቀሰቀሰ እና በታላቁ ህዳሴ ግድብም ሳቢያ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች በህብረ ብሄራት ወታደሮች ተተክተዋል።
አብዛኞቹ ሰላም አስከባሪዎች ወደኢትዮጵያ የተመለሱ ሲሆን የተወሰኑት ጥገኝነት እየጠየቁ ናቸው ሲሉ በኒው ዮርክ አንድ የተመድ ቃል አቀባይ መናገራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጠቅሶ ዘገቧል።
ብዛት ያላቸው ሰላም አስከባሪዎች መመለስ እንደማፈልጉ አስታውቀው ዓለም አቀፍ ጥበቃ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ያሉት ቃል አቀባዩ የመንግሥታቱ ድርጅት ደህንነታቸው የሚጠበቅበት ቦታ ያስቀመጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ጥገኝነት የመፍቀዱ ጉዳይ ግን በመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮምሽን ድጋፍ የሚደረግላቸው የሱዳን ባለሥልጣናት ኃላፊነት መሆኑን ቃል አቀባዩ አክለዋል።
ከኢትዮጵያውያኑ የቀድሞ ሰላም አስከባሪዎች መካከል አንዱ እና የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ሻለቃ ገብረ ኪዳኔ በጠቅላላው አምስት መቶ ሃያ ስምንት የትግራይ ተወላጅ ሰላም አስከባሪዎች ሱዳን ውስጥ ጥገኝነት እንደጠየቁ መናገራቸውን የገለጸው ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው ሁከት የሻለቃው ጓዶችም ይህንኑ ማረጋገጣቸውን ዘገባው አውስቶ የኢትዮጵያ መንግሥትን ምላሽ እንዳላገኘ አክሏል።