በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቪኦኤ ዳይሬክተር ለብሮድካስት ባለሥልጣን እርምጃ ምላሽ ሰጡ


ቪኦኤ፣ አህዱ
ቪኦኤ፣ አህዱ

አሃዱ ራዲዮና ቴሌቪዥን የአሜሪካ ድምፅ ሥርጭትን እንዳያስተላልፍ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ማዘዙ ያሳዘናቸው መሆኑን የአሜሪካ ድምፅ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዮላንዳ ሎፔዝ አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሯ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ውሳኔ አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት ምላሽ “የአሜሪካ ድምፅ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና ሁለንተናዊ ጋዜጠኛነትን የማክበር መርኆቹን አጥብቆ ይከተላል፤ ዘገባዎቻችን የኢትዮጵያን ህዝብ አስፈላጊ ጉዳዮች የሚያነሱ ናቸው” ብለዋል።

ትዕዛዙ ለኢትዮጵያዊያን የመረጃን ነፃ ፍሰትን እንደሚገድብ የጠቆሙት ሚስ ሎፔዝ “የፕሬስ ነፃነትንም ይጋፋል፤ ለሃገሪቱ ጋዜጠኞች ሁሉ አስፈሪ መልዕክት ያስተላልፋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ውሣኔውን በድጋሚ እንዲፈትሽም የቪኦኤ ዳይሬክተር ጠይቀዋል።

አሃዱ ራዲዮና ቴሌቪዥን የውጭ ሚድያ ሥርጭቶቹን ከዛሬ ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲያቋርጥ ባዘዘበት ደብዳቤ ፕሮግራሞቹን እየተቀበለ ሲያሠራጭ የቆየው “ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ” እንደሆነ ከመጠቆም በስተቀር የሰጠው የተለየ ወይም የተናጠል ምክንያት የለም።

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ደብዳቤ የደረሳቸው የአሜሪካ ድምፅ ፕሮግራሞችን ተቀብሎ ሲያሠራጭ የነበረው አሃዱ ራዲዮና ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሌሎችም የሃገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መሆናቸውን አዲስ አበባ የሚገኘው ዘጋቢያችን እስክንድር ፍሬው አረጋግጧል።

ደብዳቤው የሚድያ ተቋማቱ በገቡት የውል ግዴታና ባለፈው ዓመት በተነገረው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት “አሳዋቂ፣ አስተማሪና አዝናኝ የሆኑ አገራዊ ይዘቶችን የማሠራጨት፣ የህዝቡን ሰላምና ደኅንነት የሚያናጋ ሁኔታ ሲከሰት መግለጫዎችና መረጃዎችን የማሠራጨት እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲ ከበር የመሥራትና ራሳቸውም ህግን አክብሮ የመንቀሳቀስ ግዴታ አለባቸው” ይላል። በመገናኛ ብዙኃን ፍቃድ፣ ምዝገባና ዕውቅና ዳይሬክተር የተፈረመው ይህ ደብዳቤ ውሣኔው ጊዜያዊ ይሁን ወይም ቋሚ አይናገርም።

ጣቢያው ከባለሥልጣኑ በደረሰው ትዕዛዝ መሠረት የአሜሪካ ድምፅ ሥርጭቶችን ከዛሬ፤ ዓርብ፣ ጥቅምት 19/2021 ዓ.ም. ጀምሮ ላለተወሰነ ጊዜ እንደማያስተላልፍ ታውቋል።

XS
SM
MD
LG