በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፓርላማው ህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር እንዲነሳ ወሰነ


ፎቶ ፋይል፦ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ሜይ 7/2021 ዓ.ም በትግራይ ክልል ሃውዜን ውስጥ ሲንቀሳቀሱ። በህወሓትና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥቱ መካከል ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአራት ወራት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር እንዲሰረዝ አድርገዋል። . (ፎቶ ኤፒ)
ፎቶ ፋይል፦ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ሜይ 7/2021 ዓ.ም በትግራይ ክልል ሃውዜን ውስጥ ሲንቀሳቀሱ። በህወሓትና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥቱ መካከል ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአራት ወራት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር እንዲሰረዝ አድርገዋል። . (ፎቶ ኤፒ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ፤ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብር ዝርዝር ውስጥ እንዲነሳ በአብላጫ ድምፅ ወሰነ።

ህወሓት ከሽብርተኝነት የተሰረዘበት ውሳኔ በተላለፈበት የዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ፣ ከተወሰኑ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ውጭ ሌሎች መገናኛ ብዙኃን እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም።

ውሳኔው በ61 ተቃውሞና በአምስት ድምጸ ተአቅቦ መፅደቁን ምክር ቤቱ በፌስቡክ ገጹ ካጋራው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸውና ስማቸውን መግለፅ ያለፈለጉ ምንጮች፤ ውሳኔው ከመጽደቁ በፊት ተቃውሞ ካሰሙት የምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ የተቃውሞ አስተያየቶች መሰንዘራቸውንና ሰፊ ክርክርና ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

በተጨማሪም፣ “ስብሰባው በድንገት መጠራት አልነበረበትም፣ ስለጉዳዩ አስቀድሞ ሊነገረንና ልንዘጋጅበት ይገባ ነበር” በማለት ተቃውሞ ያሰሙ አባላት መኖራቸውንም ምንጮቻችን ገልፀዋል።

የሽብርተኝነት ውሳኔው እንዲሰረዝ የተደረገው ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ በተደረገው የሰላም ስምምነት መሰረት መሆኑ ታውቋል።

በዛሬው ስብሰባ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
በዛሬው ስብሰባ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

ምክር ቤቱ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው ጹሑፍ፤ “የሠላም ስምምነቱን ለማፅናት ህወሓትን ከሽብርተኝነት ማንሳት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ የውሳኔ ሐሳቡ በቀረበበት ወቅት ተነስቷል።”ብሏል። ዘላቂ ሠላም ለማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ም/ቤቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ( ህወሓት) የአደረጃጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን “ህወሓት ቀድሞውም አሸባሪ መባል ያልነበረበት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን በሀገሪቱ እድገት ያሰመዘገበ ፓርቲ ነው” ብለዋል:: "ውሳኔው በሕዝቡ ላይ ይደረስ የነበረው በደል የሚያስቀር ነው” ሲሉም አክለዋል::

“ለሰላም ሂደቱም ትልቅ ፋይዳ አለው” ያሉት አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን እንደ ፓርቲም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን ያለገደብ ለመፈፀም የዛሬው ውሳኔ እንደሚያግዛቸው ጨምረው ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በተደረሰው የሰላም ስምምነት አንቀጽ 7 ላይ፣ ህወሓት በተወካዮች ምክር ቤት ከተወሰነበት የሽብርተኝነት ፍረጃ እንዲነሳ የፌዴራሉ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሰፍሯል፡፡

በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከስድስት ወራት በኋላ፣ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም ነበር ህወሓትና መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” የሚለውና ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ይታወሳል፡፡

“በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ሲል” የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው ዓመታዊ የሰብዓዊ ሪፖርት ላይ ከትናንት በስትያ አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን፣ በሰጡት መግለጫ " የኢትዮጵያ መከላከያ፣ የኤርትራ መከላከያ እና የአማራ ኃይሎች ግድያን፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች እና ከቤት ንብረት ማፈናቀልን ጨምሮ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈፅመዋል" ያሉ ሲሆን ህወሓትን ግን ለነዚህ ወንጀሎች ተጠያቂ አላደረጉም፡፡

ኢትዮጵያ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ትናንት ባወጣችው የመልስ መግለጫ፣ አሜሪካ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የሰጠችው መግለጫ “ወገናዊ” እና “ተንኳሽ” ነው ስትል ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቃለች፡፡

XS
SM
MD
LG