አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት የ“ጥፋተኝነት” ውሳኔ የተላለፈበት አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት፣ ሁለተኛው ተከሳሽ ከበደ ገመቹ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ሦስተኛ ተከሳሽ አብዲ ዓለማየሁ በስድስት ወር እስራት እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍርድ ሰጥቷል።
ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም ፤ ቀደም ባለው ችሎት "ጥፋተኛ" ባላቸው ተከሳሾች ላይ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት የተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ የሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ቀደም ብሎ ያቀረባቸውን የቅጣት ማክበጃ በመቀበል የፍርድ ውሳኔውን አሳልፏል።
ዓቃቤ ሕግ ለቅጣት ማክበጃነት በሰጠው ምክኒያት፤ አቶ ጥላሁን ያሚ ከህወሃትና መንግሥት ኦነግ ሸኔ እያለ ከሚጠራቸው ታጣቂዎች ተልኮ በመቀበል ግድያ ለመፈጸም ማቀዱ፣ ተልኮውን የሰጡት ቡድኖች ደግሞ ታዋቂ ሰዎችን በመግደልና ሃገሪቱን በማሸበር መንግሥትን በኃይል ከሥልጣን ለመጣል አቅደው እንደነበር ገልጿል።
በተለይ አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ ግድያውን እንዲፈጽም ካደረጉት አካላት 1,500 የኢትዮጵያ ብር መቀበሉን፣ እንዲሁም ወደ ፊት የእርሱና የቤተሰቦቹን ሕይወት የሚቀይር ጠቀም ያል ገንዘብ እንደሚሰጠው ቃል እንደተገባለት ተከሳሹ በሰጠው ቃል ማመኑን ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል።
በተጨማሪም ተከሳሹም የራሱ የሆነ የጦር መሳርያ እያለው፣ ሟቹን አርቲስት በሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ መሳርያ ተኩሶ መግደሉ መረጋገጡን፣ “ሁለተኛ ተከሳሽም በሚኖርበት አካባቢ መልካም ጸባይ የሌለዉ እንደሆነ፣ ድርጊቱም ከፈጸመ በኋላም ለመሰወር መሞከሩ ለሕግ ተገዢ አለመሆኑን ያሳያል ሲል” ዓቃቤ ሕግ በቅጣት ማክበጃ አስተያየት ላይ አስፍሯል።
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው የፍርድ ውሳኔ ፤ አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ ባልቻ በዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ሲቀጣ፤ ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ መገርሳም በ18 ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጣ ፈርዷል።
ሦስተኛ ተከሳሽ አብዲ ዓለማየሁ በዳኔም የወንጀል ድርጊቱን ከተመለከተ በኋላ በጊዜ ለሕግ ባለማሳወቁ፣ 1ሺሕ ብርወይም የስድስት ወር ቀላል እስራት ቅጣት ወስኖበታል። ሆኖም ተከሳሹ ከስድስት ወር በላይ በማረሚያ ቤት በእስር ላይ ስለቆየ፣ በሌላ ወንጀል የማይፈለግ ካልሆነበነጻ እንዲለቀቅ ተወስኖለታል።
በዚሁ የክስ መዝገብ የቀረበችው አራተኛ ተከሳሽ ላምሮት ከማል መሃመድ ከዚህ በፊት ይህ ፍርድ ቤት በየካቲት 18፣ 2013 በቻለው ችሎት በነፃ ተሰናብታ የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ለፈደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማቅረቡ በጉዳይ ላይ የመጨረሻ ዉሳኔ ለመስጠት ለመጪው ሐምሌ 30፣ 2013 ቀጥሯል።