በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፌዴራል መንግሥቱ ኃይሎች ሽረ ገቡ፤ ጉቴሬሽ ውጊያ እንዲቆም አሳሰቡ


ፎቶ ፋይል፦ ሽረ
ፎቶ ፋይል፦ ሽረ

የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎችና አጋሮቻቸው ከትግራይ ትላልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችውን ሽረን መያዛቸውን ሮይተርስ ማምሻውን ዘገበ።

የዜና አውታሩ ለዘገባው ዋቢ ያደረገው ሁለት የዲፕሎማሲ ምንጮችን ነው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ከትግራይ አልፎ ወደ አጎራባች ክልሎችም መገንፈሉንና የኤርትራን ጦርም የቀላቀለ መሆኑን ያስታወሰው የሮይተርስ ዘገባ በሺሆች ለሚቆጠሩ ሞት፣ ለሚሊዮኖች መፈናቀልና ሊደርስ የሚችል ቸነፈር መጋለጥ ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።

ሽረ ከመቀሌ 140 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን ምዕራብ የምትገኝ ስትሆን በግጭቱ ምክንያት ከሌሎች በርካታ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሲቪሎችን ያስጠለለች ከተማ መሆኗም ይታወቃል።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ዛሬ በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ከፅህፈት ቤታቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ትግራይ ውስጥ ፀቡ በአስቸኳይ እንዲቆምና ወገኖቹ በአፍሪካ ኅብረት ወደሚመራ የሰላም ንግግር እንዲገቡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ “መዓት” ሲሉ የጠሩት ሁኔታ ፈጥኖ እንዲያበቃ ለማስቻል የመንግሥታቱ ድርጅት አህጉራዊውን ኅብረት በሚቻለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም ዋና ፀሃፊው አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኃይሎች በጣምራ የሚያካሂዱት ጥቃት ፈጥኖ እንዲቆምና ኤርትራም ከኢትዮጵያ ግዛት እንድትወጣ፣ የትግራይ ኃይሎችም ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ የአውሮፓ ኅብረት አሳስቧል።

XS
SM
MD
LG