በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የመጠጥ ውኃ ፍላጎትን ለማሟላት የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍ እንደሚገባ ተጠቆመ


በኢትዮጵያ የመጠጥ ውኃ ፍላጎትን ለማሟላት የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍ እንደሚገባ ተጠቆመ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:45 0:00

በኢትዮጵያ የመጠጥ ውኃ ፍላጎትን ለማሟላት የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍ እንደሚገባ ተጠቆመ

በውኃ ሀብት አስተዳደር እና በመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሥራዎች፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ እንደኾነ ባለሞያዎች ገለጹ፡፡ በዐዲስ አበባ በተካሔደ ዓለም አቀፍ የውኃ ሀብት ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ባለሞያዎች፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፥ በኢትዮጵያ እያደገ ያለውን የመጠጥ ውኃ ፍላጎት ለማሟላት፣ የግል ባለሀብቶች በመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና አስተዳደር ሊሳተፉ ይገባል፤ ብለዋል፡፡

ለዚኽም ደግሞ መንግሥት፣ የውኃ ሀብት ፖሊሲ ማሻሻያ ሊያደርግ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡በጉባኤው ላይ የተገኙ የውኃ እና ኤነርጂ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ደበበ ደፈርሶ፣ ይህን ሐሳብ በቀጥታ ባያንጸባርቁም፣ መንግሥት የውኃ ፖሊሲውን እያሻሻለ እንደኾነ ግን ጠቁመዋል፡፡

በዐዲስ አበባ ለሁለት ቀናት በተካሔደው የውኃ ጉባኤ፣ ልዩ ልዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ በውኃ አጠቃቀም ላይ ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል፤ ባለሞያዎችም ስለ ጉዳዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡

ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዱ የኾኑት፣ በደቡብ አፍሪካ የዩኒቨርሲቲ መምህር እና የውኃ ሀብት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰይፉ ከበደ፣ አህጉሪቱ ከፍተኛ የውኃ ሀብት ቢኖራትም፣ ወንዞቿ አመቺ ባልኾነ መልክአ ምድር ውስጥ ስለሚያልፉ፣ በቀላሉ ሊለሙ አይችሉም፤ ብለዋል፡፡

የዚኽ ዐይነት ባሕርይ ያላቸውን ወንዞች ለማልማት፣ ከፍተኛ የገንዘብ ዐቅም እንደሚጠይቅ የገለጹት ፕሮፌሰር ሰይፉ፣ ይህ ደግሞ በመንግሥታት ዐቅም የማይቻል ስለኾነ፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ እንደኾነ ያስገነዝባሉ፡፡ የግሉ ዘርፍ፣ የውኃ ሀብትን በማልማት በመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሥራም መሳተፍ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

በውኃ ሀብት አጠቃቀም እና ቁጥጥር ላይ የተለያዩ ችግሮች ይታያሉ፤ የሚሉት፣ ወተር ዊትነስ ኢንተርናሽናል የተባለ ተቋም የኢትዮጵያ ፕሮግራም ሓላፊ አቶ ኢሳይያስ ሳሙኤል በበኩላቸው፣

በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ ያለውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፍላጎት ለማሟላት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊነት ያስረዳሉ፡፡

የውኃ እና ኤነርጂ ሚኒስቴርን ወክለው በውኃ ጉባኤው ላይ የተሳተፉት አቶ ደበበ ደፈርሶ፣ መንግሥት፣ የውኃ ሀብት ፖሊሲውን እያሻሻለው እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ በሚሻሻለው የውኃ ሀብት ፖሊሲ፣ የግሉ ዘርፍ ሚና ምን ሊኾን እንደሚችል ግን አልጠቀሱም፡፡ ከዚኽ በፊት፣ ለአሜሪካ ድምፅ ቃለ መጠይቅ የሰጡት፣ የውኃ እና ኤነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ግን፣ በመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሥራ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ታሳቢ ማድረግ አስፈላጊ እንደኾነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በዐዲስ አበባ፣ ለሁለት ቀናት የተካሔደው ዓለም አቀፍ የውኃ ጉባኤ፣ ሰባት የአፍሪካ ሀገራትን አሳትፏል፡፡

XS
SM
MD
LG