በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል


የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ
የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ

የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላ ሃገሪቱ ላይ ዛሬ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አውጇል። አዋጁ ለስድስት ወራት ፀንቶ እንደሚቆይ ተደንግጓል።

“የሃገርን ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” በሚል ርዕስ በአዋጅ ቁጥር 5/2014 የወጣው ድንጋጌ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ የሃገርን ህልውና እና ሉዓላዊነት እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎችን ደኅነንት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ የፀጥታ አካል በማሠማራት ሰላምና ፀጥታ እንዲያስከብሩ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል” ይላል።

አዋጁ በመቀጠልም ዕዙ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን፣ ማናቸውም የህዝብ የመገናኛ እና የህዝብ መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ እንደሚችል ደንግጓል።

አዋጁ በዚሁ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚወሰዱ እርምጃዎች በሚለው አንቀፅ ሥር ዕዙ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ አዋጅ ተፈፃሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚችል ይናገራል።

“ተመጣጣኝ ሀይል ስለመጠቀም እና የማይታገዱ መብቶች” ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚያወጣቸው መመሪያዎች፣ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እና በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሊታገዱ የማይችሉ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን እና መብቶችን ማክበር እንደሚኖርበት” አዝዞ “የተከለከሉ ተግባራትና ግዴታዎች” ብሎ ካሠፈራቸው መካከል “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዓላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና ለሽብር ቡድኖች ዓላማ መሳካት አስተዋፅዖ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሠራጭት የተከለከለ ነው።” ይላል።

ያለቃድ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መከልከሉን፣ ያለዕውቅናና ፈቃድ ማናቸውንም የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ መከልከሉን፣ በከተሞች አካባቢ የነዋሪ መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የሠራተኛመታወቂያ፣ ፓስርፖርት ወይም ከነዚህ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን ደንግጓል።

“ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ የተከለከለ ነው” ብሏል አዋጁ።

በተጨማሪም “በአዋጁ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እሲኪጠናቀቅ ድረስ የትኛውም የዳኝነት አካል ሥልጣን እንደማይኖረው”ና “በቪዬና ኮንቬንሽን የተመለከተው የዲፕሎማቲክ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ” ከአዋጁ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ሕጎች አዋጁ ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ተፈፃሚነታቸው ታግዶ እንደሚቆይ” ደንግጓል።

የወንጀል ተጠያቂነትን በሚመለከት የሚናገረው የአዋጁ አንቀፅ ድንጋጌውንና በአዋጁ መሠረት የወጡ መመሪያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት አመት በሚደርስ ቀላል እሥራት ወይም እንደ ጥፋቱ ክብደት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት እንደሚቀጣ፣ የተፈፀመው ወንጀል በሌሎች ሕጎች ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ የከበደው ቅጣት ተፈጻሚ እንደሚሆን አመልክቷል።

በአዋጁ ላይ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ እና የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሠ ቱሉ ማብራሪያ ዛሬ ሰጥተዋል። በዚህ ዜና ላይ የአዋጁ ሙሉ ቃል አልሠፈረም።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:17 0:00


XS
SM
MD
LG