በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ 50ሺሕ ትምህርት ቤቶች ጥራታቸው ከደረጃ በታች እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታወቀ


በኢትዮጵያ 50ሺሕ ትምህርት ቤቶች ጥራታቸው ከደረጃ በታች እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:27 0:00

በኢትዮጵያ 50ሺሕ ትምህርት ቤቶች ጥራታቸው ከደረጃ በታች እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታወቀ

በኢትዮጵያ ካሉ 50ሺሕ ትምህርት ቤቶች ከፊሉ፣ በጥራታቸው ከደረጃ በታች እንደሆኑ፣ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ትምህርት ቤቶቹ፣ አስፈላጊ መሠረተ ልማት የሌላቸው ስለሆኑ፣ ለመማር ማስተማር ምቹ አይደሉም፤ ተብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ የእነዚህን ት/ቤቶች ደረጃ ማሳደግ እንደሚያስፈልግና ይህንም ለማከናወን፣ ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማሻሻል በሚደረገው ሀገራዊ ንቅናቄ፣ በአምስት ዓመት፣ የሁሉንም ት/ቤቶች ደረጃ ለመሻሻል እንደታቀደም አመልክተዋል፡፡

ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ ባለሞያዎች በበኩላቸው፣ የመምህራን ዐቅም እና የኑሮ ደረጃ አብሮ ካልተሻሻለ፣ መሠረተ ልማት ብቻውን የትምህርትን ጥራት አያረጋግጥም፤ ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አደረግኹት ያለው ጥናት፣ በኢትዮጵያ ካሉት 50ሺሕ ት/ቤቶች ውስጥ ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና ከ86 ከመቶ በላይ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ለመማር ማስተማር ሒደት የማይበጅ ከባቢ ያላቸው፣ በጥራታቸውም ከደረጃ በታች እንደሆኑ አመልክቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕር. ብርሃኑ ነጋ፣ በየጊዜው እያሽቆለቆለ ላለው የትምህርት ጥራት፣ ለመማር ማስተማሩ ምቹ ያልሆነው የትምህርት ቤቶቹ ከባቢ እና ያልተሟላ መሠረተ ልማት አስተዋፅኦ ማድረጉን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት መምህር ዶር. ከበደ ገነቲም፣ የትምህርት መሠረተ ልማት መጓደል፣ በትምህርት ጥራት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ መንግሥት፥ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሆነ ተናግረው፣ ያለበቂ የትምህርት መሠረተ ልማት፣ ጥረቱ ውጤታማ እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡ ይኹንና፣ የ50ሺሕ ት/ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ በመንግሥት ዐቅም ብቻ ስለሚያዳግት፣ በሕዝብ ንቅናቄ ለማከናወን መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት እና የትምህርት አመራር ማዕከል አስተባባሪ ዶር. ደጀኔ ንጉሤ፣ “ንቅናቄው ውጤት ሊያመጣ ይችላል” ካሉ በኋላ፣ የት/ቤቶች ግብአትም ግን አብሮ መታሰብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሀገራዊ ንቅናቄው፣ በየደረጃው ያለው ማኅበረሰብ፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ እንዲሁም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በገንዘብ እና በጉልበት ይሳተፋሉ፤ ተብሏል፡፡ ዶር. ከበደ ገነቲ በበኩላቸው፣ የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል፣ የት/ቤቶችን መሠረተ ልማት ከመገንባት ያለፈ ሥራ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡

የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻያ ሀገራዊ ንቅናቄው፣ በሚመጣው እሑድ በፌዴራል ደረጃ ተጀምሮ፣ በቀጣይ ሳምንት ደግሞ፣ በሁሉም ክልሎች እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

XS
SM
MD
LG