በናይሮቢው ሥምምነት መሰረት ለትግራይ ተዋጊዎች ገለፃ (ኦረንቴሽን) የመስጠት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና በሁለት ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ዋና አዛዡ ተናገሩ።
ዋና አዛዡ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ለክልሉ መገናኛ ብዙኋን በሰጡት መግለጫ፣ በቀጣይነት የክልሉን ተዋጊዎች ከግጭት ቦታዎች በማስወጣት ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ የማዛወር ሥራ እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡
ከመከላከያ ሰራዊቱ ውጭ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ካልወጡ በስተቀር የከባድ መሳሪያዎች ትጥቅ መፍታት ሂደት አይከናወንም ያሉት የትግራይ ተዋጊዎች ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ታደሰ፣ መከላከያ ሰራዊቱ ይህን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው የኢትዮጵያ ቡድን ኅዳር 4/2015 ዓ.ም ከናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ፣ ፊልድ ማርሻሉ በሰጡት መግለጫ ለስምምነቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
በተያያዘ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሰላም ስምምነቱን በአስቸኳይ ተግባራዊ በማድረግ አስፈላጊነትና በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
/ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ/