በድጋሚ የታደሰ፦
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ የሠላም ንግግር ዛሬም መቀጠሉን ቅርበት ያላቸውን ባለሥልጣን ጠቅሶ አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው ድርድር አንዳንድ ምሁራንና የጤና ባለሙያዎችን ግምት መሠረት በማድረግ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እልቂት ምክንያት እንደሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ያሳሰበችበትን ግጭት ለማስቆም ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ተነግሯል።
ድርድሩ ባላፈው ሣምንት ሲጀመር እስከትናንት ዕሁድ እንደሚካሄድ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ፍንጭ ሰጥተው ነበር።
ይሁን እንጂ “ድርድሩ የሚጠናቀቅበት ቀን አልተቆረጠለትም” ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ቃል አቀባይ ኤባ ካሎንዶ በላኩለት መልዕክት እንደነገሩት አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
ኤኤፍፒ አክሎም ንግግሮቹ “ነገም [ማክሰኞ] ሊቀጥሉ እንደሚችሉ” ለትግራይ ልዑካን ቅርበት ያለው ምንጭ እንደጠቆመው አመልክቷል።
በጦርነቱ ውስጥ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ኃይሎች ጎን ያሰለፈችው ኤርትራ የድርድሩ አካል አለመሆኗ የሚታወቅ ሲሆን የየትኛውም ወገን ተደራዳሪዎች እስካሁን ያወጡት መግለጫም ሆነ መረጃ እንደሌለ አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል።
ንግግሩ ከተጀመረ በኋላ እንኳ ኤርትራዊያን ሰላማዊ ሰዎችን እንደሚገድሉ እማኞች ነግረውኛል ሲል አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሲቪሎችን ዒላማ እንደማያደርጉ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ አስታውቀዋል።
በቅርቡ ሽረ አካባቢ ተደርጎ በነበረ ውጊያ በሲቪሎች ላይ ደርሷል በተባለ ጉዳይ ማዘኑን የጠቆመው የኢትዮጵያ መንግሥት ሁኔታውን እንደሚመረምርና ተጠያቂዎችን በኃላፊነት እንደሚይዝ አስታውቆ ነበር።