በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃና ሌሎችም የዛሬ ውሎ ጉዳዮች


ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

“የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ኃይሎች ትግራይ ክልል ውስጥ እያስፈፀሙ ባሉት ህግን የማስከበር ግዳጅ ሲቪሎች ላይ ጉዳት አልደረሰም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ፓርላማው ፊት ቀርበው ለእንደራሴዎች ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ የአየር ድብደባዎቹና ሌሎቹም እርምጃዎች የተወሰዱት በትክክል በተነጣጠሩና ዒላማዎቻቸውን በመቱ የተሣኩ ጥቃቶች እንደነበር፤ የህወሓትን መሪዎችም በቅርብ እየተከታተሏቸው መሆኑን ተናግረዋል።

መሪዎቹ ትናንት ምሽት ላይ ወደ አቢ አዲና አገረሰላም ሲዘልቁ በአካባቢዎቹ ላይ ጉዳይ እንዳደረሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተው ሠራዊቱ ጥቃት ያልፈፀመባቸው “ይሸሹ የነበረው ከቤተሰቦቻቸውና ከህፃናት፣ እንዲሁም ከያዟቸው የፌደራሉ ኃይል መኮንኖች ጋር በመሆኑ ነው” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተዋጊዎቻቸው አንድ የአየር ኃይል ጄት መተው መጣላቸውን የህወሓት መሪዎች ተናግረዋል። ይህንን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከሌላ ሦስተኛ ወገን የተገኘ ማረጋገጫ ለጊዜው የለም።

በተያያዘ ዜና ኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ ውስጥ ትናንት ሌሊቱን ስድስት ፍንዳታዎችን መስማታቸውን እዚያው የሚገኙት የአሜሪካ ኤምባሲ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ መቀሌን ለመያዝ በተደረገው ውጊያ የደረሰውን ጉዳይ የሚመለከት መረጃ ከባለሥልጣናቱ ባይገኝም ከተማዩቱ ውስጥ የሚገኘው አይዳር ሆስፒታል ግን የአስከሬን መከፈኛዎች እንደሌሉት ዓለምአቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ /አይሲአርሲ/ አመልክቷል።

መቀሌ የሚገኙ ሆስፒታሎች የተጎዱትን ለማከም መድኃኒት እየጨረሱ መሆናቸውን እዚያው ያሉ የተራድዖ ሠራተኞች የጠቆሙ ሲሆን ከሆስፒታል ታካሚዎች ሰማንያ ከመቶ የሚሆኑት ቀስለኞች መሆናቸውን የአይሲአርሲ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ማሪያ ሶሊዳድ ገልፀዋል።

ቀስለኞቹ ለህክምና እየተወሰዱ ያሉት ለመቀሌ ሆስፒታል ይደርስ የነበረው አቅርቦት ከተቋረጠ ከሦስት ሣምንታት በኋላ መሆኑንም ሶሊዳድ ጠቁመዋል።

በመገናኛዎች መቋረጥ ምክንያት በጦርነቱ ውስጥ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለማወቅ ለማወቅ ጋዜጠኞችና የእርዳታ ሠራተኞች የተቸገሩ ሲሆን ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሺሆች የሚቆጠር ህይወት መጥፋቱ እየተሰማ ነው።

በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ ድንበር እያቋረጡ ሱዳን ገብተዋል።

XS
SM
MD
LG