መግለጫውን በጋራ ያወጡት የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተጠሪና ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬል፣ እዲሁም የኅብረቱ ኮሚሽነሮቹ ዪታ ኡርፒላይነን እና ያኔዝ ሌናርቺች ናቸው።
ትግራይ ክልል ውስጥ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ለማድረስ የሚያስችል ሁኔታ በመጠኑ የተከፈተ መሆኑን የጠቆመው የኮሚሽነሮቹ መግለጫ ግጭቱ ሦስተኛ ወሩን ባስቆጠረበት ጊዜ የበረታ ቸነፈርንና ተጨማሪ የህይወት ጥፋትን ለማስቀረት እንዲቻል በከበደ ችግር ላይ ለሆኑ ሰዎች ለመድረስ ሁኔታው አሁንም አዳጋች መሆኑን አመልክቷል።
በማዕከላዊና ምዕራባዊ ትግራይ አብዛኛው አካባቢ ለመድረስ አስቸጋሪ መሆኑንና ክልሉ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች የተጠለሉባቸው ሁለት ሠፈሮች ሙሉ በሙሉ እንደማይደረስባቸው ኮሚሽነሮቹ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሮቹ በዚሁ የጋራ መግለጫቸው አክለው ትግራይ ክልል ውስጥ ችግር ላይ ላሉትና ክልሉ ከአማራና ከአፋር ክልሎች ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ወገንተና ያለመሆንን፣ ሰብዓዊነትን፣ ገለልተኝነትንና ነፃነትን በሚጠይቁትው የሰብዓዊነት መርኆች መሠረት እርዳታ መድረሱን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሲቪሎች እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ጥበቃ ጉዳይም የአውሮፓ ኅብረትን ይበልጥ እያሳሰበው መሆኑን ኮሚሽነሮቹ አስታውቀዋል።
በሲቪሎችና በስደተኞች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን፣ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም ስደተኞችንና ሰብዓዊነትን የሚመለከቱ ዓለምአቀፍ ህግጋት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየደረሷቸው መሆኑንም ኮሚሽነሮቹ አመልክተዋል።
ስደተኞች በዓለምአቀፍ የስደተኛ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ህግጋት መሠረት ከማናቸውም ጉዳት መጠበቅ እንዳለባቸው መግለጫው አስታውሶ ኤርትራውያን ስደተኞችን በማስፈራራት ወይም በግዳጅ ወደ ኤርትራ ለመመለስ ከሚደረግ ማናቸውም አድራጎት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስቧል።
"የአውሮፓ ኅብረትም ትግራይ ክልል ውስጥ ግጭቶችን የሚያባብሱ፣ የጭካኔ አድራጎት እንደሚፈፅሙና በብሄር ማንነት ላይ የተመሠቱ ሁከቶችንን እንደሚያደርሱ የሚከሰሱት የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከሚጠይቀው የዩናይትድ ስቴትስ ጥሪ ጎን ይቆማል" ብለዋል ኮሚሽነሮቹ።
የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እያከናወነ ያለውን ተግባር እንደሚደግፍ ኮሚሽነሮቹ ገልፀው 'ይፈፀማሉ' በተባሉት የሰብዓዊ መብቶች እና የዓለምአቀፍ ህግ ጥሰቶች ላይ ምርመራውን እንዲቀጥል እንደሚያበረታቱ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ኮሚሽኑ ያቀረባቸውን ምክር አዘል ሃሳቦች እንደሚቀበልና ጥፋተኞች ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግም የቀረቡት የነፃ ምርመራና የፍትኅ ሂደቶች መከናወናቸውን ሙሉ በሙሉ በተግባር እንደሚያውል ተስፋ እንደሚያደርጉ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ኮሚሽነሮች በጋራ መግለጫቸው ተናግረዋል።
የዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ እንዲፈቀድ የጠየቁት ኮሚሽነሮች ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞችም የደህንነት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ መርኃግብር ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ ከኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ጋር ሆነው ከትናንት በስተያ ቅዳሜ መቀሌን ጎብኝተዋል።
ዴቪድ ቢዝሊ በትዊተር ገፃቸው "ዛሬ በኢትዮጵያ ትልቅ ርምጃ ተመዝግቧል" በሚል ርዕስ ባሠፈሩት ቃል ድርጅታቸውና የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ከልል ውስጥ ሰብዓዊ ረድዔት የሚደርስበትን ሁኔታ ለማስፋፋት የሚያስችል ተጭባጭ እርምጃ ለመውሰድ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
"ቁጥሩ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው እርዳታችንን እየጠበቀ በመሆኑ ድርጅታችን እንቅስቃሴውን ያጠናክራል፤ የምናባክነው ጊዜ የለም" ብለዋል ቢዝሊ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዓለም የምግብ መርኃግብር ባወጣው መግለጫም የረድዔት ሠራተኞች ወደ ትግራይ ለመግባት ፈቃድ ለማግኘት ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተፋጠነ መንገድ ለማስተናገድ መስማማታቸውን አመልክቷል።
ትግራይ ውስጥ ለአንድ ሚሊዮን ሰው አጣዳፊ እርዳታ እንዲያቀርብና ለመድረስ አዳጋች ወደሆኑ የክልሉ ገጠራማ አካባቢዎችም መድረስ እንዲቻል የማጓጓዣ ድጋፍ እንዲያደርግ ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉንም መርኃግብሩ አስታውቋል።