በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፋር ክልል 35 ሕፃናት በድርቅ ምክኒያት ሞቱ


ድምበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን በኢትዮጵያ አፋር ክልል ስላለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታወቀ
ድምበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን በኢትዮጵያ አፋር ክልል ስላለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታወቀ

በኢትዮጵያ ሰሜን ምስራቅ በሚገኘው አፋር ክልል ውስጥ በግጭት እና ድርቅ ምክንያት 35 ሕፃናት መሞታቸውን በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች እና ድምበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን አስታወቀ።

ይህ መረጃ የወጣው አንድ የመንግሥት ሚኒስትር መስሪያ ቤት በምግብ እጥረት ምክንያት ሰዎች መሞታቸውን ካስተባበሉ ከቀናት በኋላ ነው። በኢትዮጵያ በተከታታይ ወቅቶች መጣል የነበረበት ዝናብ ባለመጣሉ በ40 ዓመት ውስጥ ያልታየ ድርቅ የተከሰተ ሲሆን በጥቅምት 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት በአፋር ክልል ከፍተኛ ውጊያን ተካሂዷል።

ድምበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ባወጣው መግለጫ ድርቅ በሚያጠቃውና ግጭት እያየለ በሄደበት የአፋር ክልል ባለፉት ስምንት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 35 ህፃናት መሞታቸውን እና ከነዚህ ውስጥ ሁለተ ሦስተኛ የሚሆኑት የሞቱት ባለፈው 48 ሰዓታት ውስጥ መሆኑን አመልክቷል።

በአዲስ አበባ የሚገኙት የቡድኑ የድንገተኛ አደጋ አስተባባሪ ራፋኤል ቬች ለአሶስዬትድ ፕሬስ ሲገልፁ "ከሁሉም በላይ የሚያሳስበን አሁን ገና የችግሩን ጫፍ ማየት መጀመራችን እና ገና ከአሁኑ ከአቅም በላይ መሆኑ ነው" ብለዋል።

ቬች አክለው "በቅርቡ በተከሰቱ ግጭቶች፣ መፈናቀል፣ የጤና አገልግሎት እጦት፣ የምግብ እና የውሃ እጥረት በቂ ካልሆነው የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ብዙ ሰዎች በአፋር ውስጥ ዝቅተኛውን የጤና እንክብካቤ፣ ምግብ እና ውሃ ማግኘት አይችሉም፣" ያሉ ሲሆን "ለተፈናቀሉ ሰዎች እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ማኅበረሰቦች የምግብ ዋስትና፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ አመጋገብ እና የውሃ አቅርቦትን ቁልፍ የትኩረት ነጥቦች በማድረግ ትልቅ የሰብአዊ ዕርዳታ ያስፈልጋል።" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ ሃገሪቱ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ አጋጥሟታል። በአፋር ክልል ትልቁ ሆስፒታል የሆነውና ከአንድ ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ዱብቲ ሆስፒታል ዳይሬክተር ሁሴን አደም የሟች ህፃናቶችን ቁጥር ለአሶስዬትድ ፕሬስ ያረጋገጡ ሲሆን ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት አብዛኞቹ ሰዎች ከትግራይ ጋር ከሚዋሰኑ አካባቢዎች እንደሆኑ ገልፀዋል።

አቶ ሁሴን "ወደ ሆስፒታላችን የሚመጡት በምግብ እጥረት የተጠቁ እና የታመሙ ህፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨምረ ነው። ይህም የሕፃናት ሞት እንዲጨምር አድርጎታል" ካሉ በኋላ የሆስፒታሉ ቡድን የተወሰኑትን ወደ ሌሎች የጤና ማዕከላት ለመላክ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም "ሆስፒታላችን በመሙላት ድንኳኖችን እየተጠቀምን ነው። ግን እሱም አሁን ሙሉ በመሆኑ የተወሰኑትን የምናክመው በመተላለፊያ ኮሪደሮች ላይ ነው።” ብለዋል።

ድምበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በመግለጫው በአፋር ክልል ከሚገኙ የጤና ተቋማት ብዙዎቹ የተበላሹ፣ የወደሙ፣ የተተው ወይም በቂ የህክምና መሳሪያዎች የሌላቸው መሆኑን ጠቅሶ በጥቅሉ 20 በመቶው ብቻ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የገለፀ ሲሆን "በዱፕቲ ሆስፒታል፣ ከ80 በመቶ በላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካለባቸው ህጻናት ወደ ሪፈራል ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የጤና አገልግሎት አግኝተው የማያውቁ ናቸው" ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጧቸው መረጃዎች በሌሎች የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያኖችም የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ያሳያል።

የኢትዮጵያ ፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ፍፁም አሰፋ ሰኞ ዕለት ለካቢኔ አባላት ባቀረቡት ሪፖርት በደቡብ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሊያ ክልልሎች የሚገኙ 7.4 ሚሊየን ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል። "በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሚገኙ 5.2 ሚሊየን፣ በአፋር 600 ሺሕ እንዲሁም በአማራ ክልል 8.7 ሚሊየን ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና በመንግሥት እና እርዳታ ሰጪ አካላት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው" ሲሉ ሚኒስትሯ አስረድተዋል። ሆኖም ሚኒስትሯ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ያስተባበሉ ሲሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት 'ትልቅ ስኬት' ሲሉ ገልፀውታል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር የካቲት ወር ላይ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ድርቅ ያስከተለው ረሃብ በሶማሌ እና በቦረና አካባቢዎች

"የህፃናት እና የአዛውንትን ሕይወት እየቀጠፈ ነው" ሲሉ ገልፀው ነበር። አክለውም "የዝናቡ ወቅት እስኪመለስ የምንጠብቅ ከሆነ ተጨማሪ ዜጎቻችንን እናጣለን" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ የሚገኙ 4.2 ሚሊየን ሰዎችን ለመርዳት 846 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው ማክሰኞ እለት ያስታወቀ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ህፃናት መሆናቸውን አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG