በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ


ፎቶ ፋይል፦ አቶ ጌታቸው ረዳ
ፎቶ ፋይል፦ አቶ ጌታቸው ረዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የህወሓት ቃል አቀባይና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾመዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በፌስ ቡክ ገጹ እንዳስታወቀው “ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ውክልና የሚያረጋግጥ እና አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈጻሚ አካል የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል” ብሏል፡፡

ጽህፈት ቤቱ አክሎም በመንግሥትና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ሥምምነት መሠረትና የሚኒስትሮች ም/ቤት ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 9፣ 2015 ባጸደቀው “የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ድንብ” ማጽደቁን ገልጿል፡፡

ሹመቱ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብር ዝርዝር ውስጥ እንዲነሳ ትናንት በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ የመጣ ነው።

ም/ቤቱ ትናንት ባደረገው ልዩ ስብሰባ በ61 ተቃውሞና በ5 ድምጸ ተአቅቦ ውሳኔውን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ህወሓት ከሽብርተኝነት እንዲነሳ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ፣ ከምክር ቤት አባላት “ጠንካራ የተቃውሞ አስተያየቶች” መሰንዘራቸውን የአሜሪካ ድምጽ ከውስጥ ምንጮች መረዳት ችሏል፡፡

ባለፈው ጥቅምት በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት “ለማጽናት ህወሓትን ከሽብርተኝነት ማንሳት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ የውሳኔ ሃሳቡ በቀረበበት ወቅት ተነስቷል” ብሏል ም/ቤቱ በፌስቡክ በለቀቀው መልዕክት፡፡

XS
SM
MD
LG